የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 1:1-18

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 1:1-18 አማ05

በኮረብታማው በኤፍሬም አገር ራማ ተብላ በምትጠራ ትንሽ ከተማ የሚኖር ትውልዱ ከኤፍሬም ነገድ የሆነ፥ ሕልቃና ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም የይሮሐም ልጅ የኤሊሁ የልጅ ልጅ ሲሆን፥ ኤሊሁ ደግሞ የቶሑ ልጅ የጹፍ የልጅ ልጅ ነበር፤ ሕልቃናም ሐናና ፍኒና ተብለው የሚጠሩ ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ፍኒና ልጆች ነበሩአት፤ ሐና ግን አንድም ልጅ አልነበራትም፤ ሕልቃና በየዓመቱ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ለመስገድና መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ሴሎ ይሄድ ነበር፤ በዚያም ዘመን ሖፍኒና ፊንሐስ ተብለው የሚጠሩት የዔሊ ልጆች የእግዚአብሔር ካህናት ሆነው በሴሎ ያገለግሉ ነበር። ሕልቃና መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ ከመሥዋዕቱ ሥጋ አንድ ድርሻ ለጵኒና ይሰጣል፤ እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ለእያንዳንዳቸው አንዳንድ ድርሻ ያድላል፤ ሐናን ይወዳት ስለ ነበር እጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ቢሆንም እግዚአብሔር ልጅ ስላልሰጣት መኻን ነበረች፤ እግዚአብሔርም ልጅ ስላልሰጣት ጣውንትዋ ጵኒና ሐናን የሚያስቈጣ ነገር በመፈለግ ታበሳጫት ነበር፤ ይህም ሳይቋረጥ በየዓመቱ የሚደጋገም ነገር ነበር፤ ይኸውም ወደ እግዚአብሔር ቤት በሄዱ ቊጥር ሐና እያለቀሰች ምግብ ለመብላት እምቢ እስከምትል ድረስ ጵኒና በብርቱ ታበሳጫት ነበር። ከዚህም የተነሣ ባልዋ ሕልቃና “ሐና ሆይ! ስለምን ታለቅሻለሽ? ስለምንስ አትመገቢም? ስለምንስ ዘወትር ይህን ያኽል ታዝኚአለሽ? ከዐሥር ልጆች ይልቅ እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር። አንድ ቀን በሴሎ መሥዋዕት ሠውተው ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሣች፤ ካህኑም ዔሊ በእግዚአብሔር መቅደስ በር አጠገብ ተቀምጦ ነበር። እርስዋም ከልብዋ ሐዘን የተነሣ ምርር ብላ እያለቀሰች ወደ እግዚአብሔር ጸለየች። ሐናም እንዲህ ስትል ስእለት ተሳለች፦ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እኔን አገልጋይህን ተመልከተኝ! መከራዬንም በማየት አስበኝ! አትርሳኝም! አንድ ወንድ ልጅ ብትሰጠኝ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለአንተ የተለየ እንዲሆን አደርገዋለሁ፤ ጠጒሩም ከቶ አይላጭም።” ሐና በዚህ ዐይነት ጸሎትዋን በማስረዘም ብዙ ጊዜ ስለ ቈየች፥ ዔሊ አፍዋን ይመለከት ነበር፤ ሐና ምንም ድምፅ ሳታሰማ ከንፈርዋን እያንቀሳቀሰች በልብዋ በመናገር ትጸልይ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ዔሊ በመጠጥ የሰከረች መሰለው፤ “እንዲህ ሰክረሽ የምትቈዪው እስከ መቼ ነው? ይህን ስካርሽን ወዲያ አስወግጂ!” አላት። እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰችለት፦ “አይደለም ጌታዬ ሆይ! እኔ በጥልቅ ሐዘን ላይ ያለሁ ሰው ነኝ፤ ወይን ጠጅም ሆነ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም፤ ነገር ግን ችግሬን ለእግዚአብሔር እያቀረብኩ ነው። እኔን አገልጋይህን እንደማትረባ ሴት አድርገህ አትቊጠረኝ፤ ይህን ያኽል በማስረዘም የጸለይኩት መከራ የበዛብኝ ችግረኛ በመሆኔ ነው።” ዔሊም “በሰላም ሂጂ! የእስራኤል አምልክ የለመንሽውን ይስጥሽ!” አላት። እርስዋም “እኔን አገልጋይህን በጸሎትህ አስበኝ!” አለችው፤ ከዚያም ተነሥታ በመሄድ ምግብ ተመገበች፤ ሐዘንዋንም አቆመች።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}