ስለዚህ ልቡናችሁን አንቅታችሁ ለሥራ ተዘጋጁ፤ በመጠን ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ለምታገኙት ጸጋ ሙሉ ተስፋ ይኑራችሁ። ታዛዦች ልጆች ሆናችሁ ባለማወቅ ቀድሞ የነበራችሁን ክፉ ምኞት አትከተሉ፤ ነገር ግን የጠራችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ “እኔ ቅዱስ ስለ ሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፎአል። ለማንም ሳያዳላ ለያንዳንዱ እንደየሥራው የሚፈርደውን እግዚአብሔርን “አባታችን” ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ በዚህ ዓለም በእንግድነት መጻተኞች ሆናችሁ ስትኖሩ እርሱን በመፍራት ኑሩ። እናንተ ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ አኗኗር የተዋጃችሁት ጠፊ በሆነ በብር ወይም በወርቅ አለመሆኑን ታውቃላችሁ። እናንተ የተዋጃችሁት ነውር ወይም እንከን እንደሌለው ንጹሕ በግ በሆነው በክርስቶስ ክቡር ደም ነው። እርሱ የታወቀው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን፥ አሁን በመጨረሻው ዘመን ስለ እናንተ ተገልጦአል። እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ በኢየሱስ አማካይነት እርሱን ከሞት ባስነሣውና ክብርን በሰጠው በእግዚአብሔር ትተማመናላችሁ። ለምእመናን ቅንነት የተሞላበት ፍቅር እንዲኖራችሁ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን አንጽታችኋል፤ ስለዚህ በሙሉ ልባችሁ እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። ዳግመኛ የተወለዳችሁት ሕያው በሆነውና ለዘለዓለም ጸንቶ በሚኖረው በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ መጽሐፍ እንደሚለው፦ “ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ዱር አበባ ነው፤ ሣሩም ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።” የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይኸው ነው።
1 የጴጥሮስ መልእክት 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 የጴጥሮስ መልእክት 1:13-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos