የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 21

21
የናቡቴ የወይን ተክል ቦታ
1ናቡቴ ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም በኢይዝራኤል በሚገኘው በንጉሥ አክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ የራሱ ርስት የሆነ አንድ የወይን ተክል ቦታ ነበረው። 2አንድ ቀን አክዓብ ናቡቴን “የወይን ተክል ቦታህን ስጠኝ፤ በቤተ መንግሥቴ አጠገብ ስለ ሆነ የአትክልት ቦታ ላደርገው እፈልጋለሁ፤ በምትኩ ከእርሱ የተሻለ የወይን ተክል ቦታ እሰጥሃለሁ፤ ልትሸጠው ብትፈልግም የተሻለ ጥሩ ዋጋ እከፍልሃለሁ” አለው።
3ናቡቴም “ይህን የወይን ተክል ቦታ የወረስኩት ከቀድሞ አያቶቼ ነው፤ ለአንተ ከመስጠትስ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ!” ሲል መለሰለት።
4አክዓብ፥ የእዝራኤላዊው ናቡቴ “ከአባቶቼ የወረስኩትን ለአንተ አልሰጥህም!” ስላለው በንዴት እየተበሳጨ ወደ ቤቱ ገባ፤ ፊቱንም ወደ ግድግዳ አዙሮ በአልጋው ላይ ተጋደመ፤ ምግብ መብላትም አልፈቀደም። 5ሚስቱም ኤልዛቤል ወደ እርሱ ቀርባ “እንደዚህ ያበሳጨህ ነገር ምንድን ነው? ስለምንስ ምግብ አትበላም?” ስትል ጠየቀችው።
6እርሱም “እኔን ያበሳጨኝ ከናቡቴ ያገኘሁት መልስ ነው፤ ይኸውም የእርሱን የወይን ተክል ቦታ እንድገዛ ወይም ከፈለገ ልዋጩን እንድሰጠው ብጠይቀው የወይን ተክል ቦታውን ‘በምንም ዐይነት አልሰጥህም’ ብሎ አናደደኝ” ሲል መለሰላት።
7ኤልዛቤልም “እንግዲህ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ሆነህ ሳለህ እንደዚህ መሆን ይገባሃልን? ይልቅስ ተነሥ፤ በመደሰትም እህል ውሃ ቅመስ፤ እኔ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ እንድታገኝ አደርጋለሁ!” አለችው።
8ከዚህም በኋላ እርስዋ ደብዳቤ ጽፋ በአክዓብ ስም ፈርማ የእርሱኑ ማኅተም አተመችበት፤ ደብዳቤውንም ናቡቴ ወደሚኖርባት ወደ ኢይዝራኤል ባለሥልጣኖችና ሽማግሌዎች ላከች። 9ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፦ “የአንድ ቀን ጾም ዐውጁ፤ ሕዝቡንም በአንድነት ሰብስቡ፤ ለናቡቴም የክብር ቦታ ስጡት፤ 10‘እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል’ ብለው የሚናገሩ ሁለት የሐሰት ምስክሮችንም አቅርቡ፤ ከዚያም በኋላ ናቡቴን ከከተማው ውጪ አውጥታችሁ በድንጋይ በመውገር ግደሉት።”
11የኢይዝራኤል ባለሥልጣኖችና ሽማግሌዎችም ኤልዛቤል ያዘዘቻቸውን አደረጉ፤ 12የአንድ ቀን ጾም ዐወጁ፤ ሕዝቡንም በአንድነት ሰበሰቡ፤ ለናቡቴም የክብር ቦታ ሰጡት፤ 13ሁለቱም የሐሰት ምስክሮች ተነሥተው “ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቦአል” ብለው በሕዝቡ ፊት በሐሰት መሰከሩበት፤ ስለዚህም ከከተማይቱ ውጪ በመውሰድ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። 14“ናቡቴ ተወግሮ ተገድሎአል” የሚል መልእክትም ወደ ኤልዛቤል ላኩ።
15ኤልዛቤልም መልእክቱን እንደ ተቀበለች ወዲያውኑ አክዓብን “ናቡቴ ሞቶአል፤ በል አሁን ተነሥተህ ሂድና ለአንተ ለመሸጥ እምቢ ያለውን የወይን ተክል ቦታ ርስት አድርገህ ውሰድ” አለችው። 16አክዓብም የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ ለመውረስ ወዲያውኑ ተነሥቶ ሄደ።
17ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቲስቢያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18“ወደ ሰማርያው ንጉሥ ወደ አክዓብ ሂድ፤ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በመውረስ ላይ እንዳለ በዚያው ታገኘዋለህ፤ 19እኔ እግዚአብሔር ስለ እርሱ የምለው ይህ ነው ‘ናቡቴን መግደልህ አንሶህ ሀብቱንም ልትወርስበት ነውን?’ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ እንዲሁም የአንተን ደም ይልሱታል!’ ” #1ነገ. 22፥38።
20አክዓብ ኤልያስን ባየው ጊዜ “ጠላቴ ሆይ! አገኘኸኝን?” አለው።
ኤልያስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አዎ! አግኝቼሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ራስህን ለኃጢአት ሸጠሃል፤ 21ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል፦ ‘እነሆ በአንተ ላይ መቅሠፍትን አመጣብሃለሁ፤ አንተን ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ ከቤተሰብህም ውስጥ ወንድ የሆነውን ሁሉ ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አጠፋለሁ። 22እስራኤልን ወደ ኃጢአት በመምራታችሁ ቊጣዬን ስለ አነሣሣህ ቤተሰብህን እንደ ናባጥ እንደ ንጉሥ ኢዮርብዓም ቤተሰብና እንደ አኪያ ልጅ እንደ ንጉሥ ባዕሻ ቤተሰብ ለማጥፋት የተጋለጠ ይሆናል። 23ስለ ኤልዛቤልም እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ ሬሳዋን በኢይዝራኤል ከተማ ውስጥ ውሾች ይበሉታል፤ #2ነገ. 9፥36። 24ከዘመዶችህ መካከል በከተማው ውስጥ የሚሞተውን ማንኛውንም ሰው ውሾች ይበሉታል፤ በገጠርም በየሜዳው የሚሞተውን ሁሉ አሞራዎች ይበሉታል።’ ”
25በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር በማድረግ ሁለንተናውን ለኃጢአት አሳልፎ የሸጠ አክዓብን የሚምስል ማንም አልነበረም፤ ይህን ሁሉ ለማድረግ የተገደደው ሚስቱ ኤልዛቤል ወደ ክፋት ስለ መራችው ነው፤ 26አክዓብ ከፈጸመው አሳፋሪ በደል ሁሉ ዋናው ክፍል እስራኤላውያን ወደ ምድረ ርስት በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ከፊታቸው ነቃቅሎ ያባረራቸው አሞራውያን ያደርጉት በነበረው ዐይነት ጣዖት ማምለኩ ነው።
27ኤልያስ ንግግሩን ከፈጸመ በኋላ አክዓብ ልብሱን በመቅደድና አውልቆ በመጣል ማቅ ለበሰ፤ እህል መቅመስንም እምቢ አለ፤ ማቁንም እንደ ለበሰ ይተኛ ነበር፤ ሲሄድም ከጭንቀቱ ብዛት የተነሣ ፊቱ ጠቊሮ ይታይ ነበር።
28የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ቴስቢያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 29“አክዓብ በእኔ ፊት ራሱን እንዴት እንዳዋረደ ተመልክተሃልን? ይህን ስላደረገ በሕይወቱ ሳለ መቅሠፍትን አላመጣበትም፤ የተባለውን መቅሠፍት በአክዓብ ቤተሰብ ላይ የማመጣው በልጁ የሕይወት ዘመን ይሆናል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ