የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8:4-13

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8:4-13 አማ05

ስለዚህ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት የሆነ እንደ ሆነ ጣዖት ሕይወት የሌለው እንደ ሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። ምንም እንኳ አምላክ ሳይሆኑ አማልክት ተብለው የሚጠሩ ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች በሰማይም ሆነ በምድር አሉ ቢባል የእኛ አምላክ ግን የሁሉ ነገር ፈጣሪና እኛም የእርሱ የሆንን አንዱ እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው፤ እንዲሁም ሁሉ ነገር በእርሱ የተፈጠረና እኛም በእርሱ የምንኖር አንዱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ነገር ግን ይህን የሚያውቁ፥ ሁሉም አይደሉም፤ አንዳንዶች እስከ አሁን ድረስ ጣዖትን ማምለክ ስለ ለመዱ ሥጋን የሚበሉት ለጣዖት እንደ ተሠዋ አድርገው ነው፤ ስለዚህ ኅሊናቸው ደካማ በመሆኑ ይረክሳሉ። ዳሩ ግን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን መብል አይደለም፤ ባንበላም የሚጐድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ይህ ነጻነታችሁ በእምነት ላልጠነከሩ ሰዎች መሰናከያ እንዳይሆንባቸው ተጠንቀቁ። “ዕውቀት አለኝ” ብለህ ለጣዖት የተሠዋውን በቤተ ጣዖት ስትበላ በእምነቱ ያልጠነከረ ሰው ቢያይህ ይህ ድርጊትህ ሰውየው ለጣዖት የተሠዋውን እንዲበላ ያደፋፍረው የለምን? ስለዚህ በአንተ “ዐዋቂ ነኝ” ባይነት ክርስቶስ የሞተለትና በእምነቱ ያልጠነከረ ክርስቲያን ይጠፋል ማለት ነው። በዚሁ ሁኔታ ክርስቲያን ወንድሞቻችሁን በመበደልና ደካማ ኅሊናቸውንም በማቊሰል ክርስቶስን ትበድላላችሁ። ስለዚህ ምግብ ክርስቲያን ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከቶ ሥጋ አልበላም።