የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2

2
ስለተሰቀለው ክርስቶስ ማስተማር
1ወንድሞቼ ሆይ! እኔ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር የመሰከርኩት የንግግርን ችሎታና የፍልስፍናን ጥበብ በማሳየት አይደለም። #2፥1 ስለ እግዚአብሔር መመስከር፦ አንዳንድ የብራና ጽሑፎች “ስለ እግዚአብሔር ምሥጢር ማስተማር” ይላሉ። 2ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር በተለይም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞቱን በቀር ሌላ ምንም ነገር ላለማወቅ ወስኜ ነበር። 3ስለዚህ ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ደካማ ሆኜ በፍርሃትና በብዙ መንቀጥቀጥ ላይ ነበርኩ። 4ንግግሬና ስብከቴ በሰብአዊ ጥበብና ንግግር በማሳመር ሳይሆን በእግዚአብሔር መንፈስ ኀይል የተደገፈ ነበር። 5ይህንንም ያደረግኹት እምነታችሁ በሰው ጥበብ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በእግዚአብሔር ኀይል የተደገፈ እንዲሆን ነው።
የእግዚአብሔር ጥበብ
6ነገር ግን በመንፈሳዊ ሕይወት ለበሰሉት በጥበብ ቃል እንናገራለን፤ ይሁን እንጂ የምንናገረው የዚህን ዓለም ጥበብ ወይም መጨረሻቸው ጥፋት የሚሆነውን የዚህን ዓለም ገዢዎች ጥበብ አይደለም። 7እኛ የምንናገረው ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን ያዘጋጀውንና ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ምሥጢር ጥበብ ነው። 8ከዚህ ዓለም ገዢዎች መካከል ይህን ጥበብ ያወቀ ማንም የለም፤ ዐውቀውትስ ቢሆን ኖሮ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር። 9ይሁን እንጂ መጽሐፍ፥
“የሰው ዐይን ያላየውን፥
የሰው ጆሮ ያልሰማውን፥
የሰው ልብ ያላሰበውን፥
እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቶአል” ይላል። #ኢሳ. 64፥4።
10ለእኛ ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካይነት ምሥጢሩን ገልጦልናል፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ምሥጢር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ነገር ይመረምራል። 11ስለ ሰው የሆነ እንደ ሆነ ከገዛ ራሱ መንፈስ በቀር በእርሱ ያለውን ሐሳብ የሚያውቅ ማን ነው? እንዲሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን አሳብ የሚያውቅ ማንም የለም። 12ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ነገር እንድናውቅ የእግዚአብሔርን መንፈስ እንጂ የዚህን ዓለም መንፈስ አልተቀበልንም።
13ስለዚህ እኛ መንፈሳዊውን ነገር ለመንፈሳውያን ሰዎች የምናስተምረው ከሰው በሚገኘው ጥበብ ሳይሆን ከእግዚአብሔር መንፈስ በሚገኘው ጥበብ ነው። 14የእግዚአብሔር መንፈስ የሌለው ሥጋዊ ሰው ግን ከእግዚአብሔር መንፈስ የሚሰጠውን ስጦታ መቀበል አይችልም፤ የስጦታው ታላቅነት የሚመረመረው በእግዚአብሔር መንፈስ አማካይነት ስለ ሆነ ሊያስተውለው አይችልም፤ እንዲያውም ይህ ለእርሱ ሞኝነት መስሎ ይታየዋል። 15የእግዚአብሔር መንፈስ ያለው ግን ሁሉን ነገር መመርመር ይችላል፤ እርሱ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም። 16ይህም፦
“የጌታን ሐሳብ ማን ሊያውቀው ይችላል?
ሊመክረውስ የሚችል ማን ነው?” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።
እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን። #ኢሳ. 40፥13።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ