የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 22

22
1ዳዊትም “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና የእስራኤል ሕዝብ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርቡበት መሠዊያ ሊኖሩ የሚገባቸው በዚህ ስፍራ ነው” አለ።
ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት
2ንጉሥ ዳዊት በእስራኤል ምድር የሚኖሩትን መጻተኞች በአንድነት ሰብስቦ በሥራ ላይ እንዲሰማሩ አደረገ፤ ከእነርሱ አንዳንዶቹ ለቤተ መቅደሱ መሥሪያ እንዲሆን ድንጋይ ጠራቢዎችን መደበ፤ 3ዳዊት ለቅጽር በሮቹ መሥሪያ የሚሆን ምስማርና ማጠፊያ የሚሠራበት ብዙ ብረት፥ እንዲሁም የክብደቱ ሚዛን እጅግ ብዙ የሆነ ነሐስ አዘጋጀ፤ 4የጢሮስና የሲዶን ሕዝብ ቊጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ የሊባኖስ ዛፍ ግንድ እንዲያመጡለት አደረገ። 5ዳዊት “ልጄ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር የሚሠራው ቤተ መቅደስ እጅግ የተዋበና በዓለም ዝነኛ መሆን ይገባዋል፤ ነገር ግን እርሱ ገና ልጅና በዕውቀትም ያልበሰለ በመሆኑ፥ እኔ ሁሉን ነገር አዘጋጅለታለሁ” ሲል በልቡ አሰበ፤ ስለዚህም ዳዊት ከመሞቱ በፊት ብዙ የቤት መሥሪያ ዕቃዎችን አዘጋጀ።
6ዳዊት ልጁን ሰሎሞንን አስጠርቶ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲሠራ አዘዘው፤ 7እንዲህም አለው፤ “ልጄ ሆይ፥ እኔ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቤ አስቤ ነበር፤ 8እግዚአብሔር ግን ‘አንተ ብዙ ሰው ገድለሃል፤ በብዙ ጦርነቶችም ላይ ውጊያ አድርገሃል፤ ብዙ ደም በማፍሰስህም ቤተ መቅደስ እንድትሠራ አልፈቅድልህም’ ብሎኛል፤ 9ይሁን እንጂ እንዲህ በማለት የተስፋ ቃል ሰጥቶኛል፥ ‘እኔ ከጠላቶቹ ሁሉ አሳርፌ ሰላም ስለምሰጠው በሰላም የሚያስተዳድር ወንድ ልጅ ይኖርሃል፤ በእርሱ ዘመነ መንግሥት ለእስራኤል ሰላምና ጸጥታ ስለምሰጥ ስሙ ሰሎሞን ተብሎ ይጠራል፤ 10ለእኔ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ እርሱ ነው፤ እርሱ ልጅ ይሆነኛል፤ እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ መንግሥቱም በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።’ ” #2ሳሙ. 7፥1-16፤ 1ዜ.መ. 17፥1-14።
11ዳዊት ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “አሁንም ልጄ ሆይ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ ለእርሱ ቤተ መቅደስ ትሠራለት ዘንድ የሰጠውን የተስፋ ቃል በመጠበቅ ሁሉን ነገር ያከናውንልህ፤ 12በእስራኤል ላይ ሥልጣን በሚሰጥህ ጊዜ ያምላክህን የእግዚአብሔርን ሕግ ትጠብቅ ዘንድ ጥበቡንና ማስተዋሉን ይስጥህ፤ 13እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል የሰጠውን ሕጎችንና ሥርዓቶችን ሁሉ ብትፈጽም፥ ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤ በርታ፤ ቈራጥ ሁን፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቊረጥ። #ኢያሱ 1፥6-9። 14ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ የሆነ እንደሆን፥ በበኩሌ ለሕንጻ ሥራ የሚውል ሦስት ሺህ አራት መቶ ቶን ወርቅና ከሠላሳ አራት ሺህ ቶን በላይ የሚሆን ብር አከማችቼልሃለሁ፤ በተጨማሪም ስፍር ቊጥር የሌለው ነሐስና ብረት አዘጋጅቼልሃለሁ፤ እንዲሁም እንጨትና ድንጋይ አዘጋጅቼልሃለሁ፤ ይሁን እንጂ አንተም በተጨማሪ ማግኘት አለብህ፤ 15አንተ ብዙ ሠራተኞች ድንጋይ የሚፈልጡ፥ ግንበኞችና አናጢዎች፥ እንዲሁም ባለሙያዎች በየዐይነቱ አሉልህ፤ 16በወርቅ፥ በብር፥ በነሐስና በብረት ሥራ የታወቁ ልዩ ልዩ ሙያ ያላቸው ሰዎች አሉህ፤ እንግዲህ አሁን ሥራህን ጀምር፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን።”
17ዳዊት የእስራኤል መሪዎች በሙሉ ልጁን ሰሎሞንን ይረዱት ዘንድ ትእዛዝ በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ 18“አምላካችሁ እግዚአብሔር እስከ አሁን ከእናንተ ጋር አይደለምን? በሁሉም አቅጣጫ ሰላምን ሰጥቶአችሁ የለምን? በዚህች ምድር ላይ ይኖሩ የነበሩትን ሕዝቦች ሁሉ ድል አድርጌ እንድይዛቸው ፈቅዶልኛል፤ እነርሱም ለእናንተና ለእግዚአብሔር ተገዢዎች ሆነዋል፤ 19እንግዲህ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ አገልግሉ፤ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦትና እግዚአብሔርን ለማምለክ መገልገያ የሆኑትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አምጥታችሁ በውስጡ ማኖር ትችሉ ዘንድ ቤተ መቅደሱን ለክብሩ መሥራት ጀምሩ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ