የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 18

18
ዳዊት በጦርነት የተቀዳጃቸው ድሎች
(2ሳሙ. 8፥1-18)
1ጥቂት ዘግየት ብሎም ንጉሥ ዳዊት እንደገና በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ በመጣል ድል አደረጋቸው፤ አስገበራቸውም፤ የጋትን ከተማና በዙሪያዋ ያሉትን መንደሮች ከእነርሱ ቊጥጥር ነጻ አደረገ፤ 2ሞአባውያንንም ድል ነሥቶ እንዲገብሩለት አደረገ።
3ቀጥሎም ንጉሥ ዳዊት በሶርያ አገር እስከ ሐማት ግዛት አጠገብ በምትገኘው በጾባ ንጉሥ በሀዳድዔዜር ላይ አደጋ ጣለ፤ ይህንንም ያደረገው ሀዳድዔዜር ከላይ በኩል በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ያለውን ግዛት በቊጥጥሩ ሥር ለማድረግ ዘምቶ ስለ ነበር ነው፤ 4ዳዊት የሀዳድዔዜርን አንድ ሺህ ሠረገሎች፥ ሰባት ሺህ ፈረሰኞችና ኻያ ሺህ እግረኛ ሠራዊት ማረከ፤ አንድ መቶ ሠረገላ የሚጐትቱ ፈረሶችን ለራሱ አስቀርቶ የቀሩትን ፈረሶች ቋንጃ ቈረጠ።
5በደማስቆ ያሉ ሶርያውያን የጾባን ንጉሥ ሀዳድዔዜርን ለመርዳት ሠራዊት በላኩ ጊዜ ዳዊት በእነርሱም ላይ አደጋ ጥሎ ኻያ ሁለት ሺህ ወታደሮችን ገደለ፤ 6ከዚያም በኋላ በግዛታቸው ላይ የጦር ሰፈር አቋቋመ፤ ሕዝቡም ግብር እየከፈለ ለእርሱ ተገዛ፤ እግዚአብሔር ዳዊትን በየስፍራው ድል አድራጊ አደረገው፤ 7ዳዊት የሀዳድዔዜር ባለሟሎች የሆኑ ባለሥልጣኖች አንግበውት የነበረውን ከወርቅ የተሠራ ጋሻ ሁሉ ማርኮ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው፤ 8እንዲሁም የሀዳድዔዜር ግዛት ከነበሩት ከጢብሐትና ከኩን ከተማዎች እጅግ ብዙ የሆነ ነሐስ ወሰደ፤ ዘግየት ብሎም ሰሎሞን በነሐሱ የቤተ መቅደሱን ገንዳ፥ ዐምዶችና የነሐስ ዕቃዎች አሠራበት። #1ነገ. 7፥40-47፤ 2ዜ.መ. 4፥11-18።
9የሐማት ንጉሥ ቶዒ ዳዊት የጾባን ንጉሥ የሀዳድዔዜርን መላ ሠራዊት ድል እንዳደረገ ሰምቶ 10ቶዒ ከሀዳድዔዜር ጋር ብዙ ጊዜ ጦርነት አድርጎ ስለ ነበር፥ ንጉሥ ዳዊትን እጅ እንዲነሣና በሀዳድዔዜር ላይ ስለ ተቀዳጀው ድል ደስታውን እንዲገልጥለት ልጁን ዮራምን ወደ ዳዊት ላከ። ዮራምም ከወርቅ፥ ከብርና ከነሐስ የተሠሩ ዕቃዎችን ገጸ በረከት አድርጎ ለዳዊት አመጣለት፤ 11ንጉሥ ዳዊትም እነርሱን ወስዶ ከኤዶም፥ ከሞአብ፥ ከዐሞን፥ ከፍልስጥኤምና ከዐማሌቅ ሕዝቦች ማርኮ ካመጣቸው ከወርቅ፥ ከብርና ከነሐስ ከተሠሩ ዕቃዎች ጋር ለአምልኮ ሥነ ሥርዓት መገልገያ እንዲሆኑ አደረጋቸው።
12የጸሩያ ልጅ አቢሳ ኤዶማውያንን በጨው ሸለቆ ውስጥ ድል አድርጎ ከእነርሱ መካከል ዐሥራ ስምንት ሺህ የሚሆኑትን ገደለ፤ #መዝ. 60። 13በመላው የኤዶም ግዛት ውስጥ የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ በዚያም የሚኖሩ ሰዎች የንጉሥ ዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ እግዚአብሔር ዳዊትን በሁሉ ስፍራ ድል አድራጊ አደረገው።
14ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሕዝቡም ሁልጊዜ አድልዎ የሌለበት ፍትሕ እንዲያገኙ አደረገ። 15የአቢሳ ወንድም ኢዮአብ የሠራዊቱ አዛዥ ነበር፤ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ የቤተ መዛግብት ኀላፊ ነበር፤ 16የአሒጡብ ልጅ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አቤሜሌክ ካህናት ነበሩ፤ ሱሳ የቤተ መንግሥት ጸሐፊ ነበር፤ 17የዮዳሄ ልጅ በናያ የዳዊት ክብር ዘብ አዛዥ ነበር፤ የንጉሥ ዳዊት ወንዶች ልጆች በአባታቸው መንግሥት ከፍተኛ ማዕርግ ነበራቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ