የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሶፎንያስ 3

3
የኢየሩሳሌም የወደ ፊት ዕጣ
1ለዐመፀኛዪቱና ለረከሰች፣
ለጨቋኞች ከተማ ወዮላት!
2እርሷ ለማንም አትታዘዝም፤
የማንንም ዕርምት አትቀበልም፤
እግዚአብሔር አትታመንም፤
ወደ አምላኳም አትቀርብም።
3ሹሞቿ የሚያገሡ አንበሶች፣
ገዦቿ ለነገ የማይሉ፣
የምሽት ተኵላዎች ናቸው።
4ነቢያቷ ትዕቢተኞች፣
አታላዮችም ናቸው፤
ካህናቷ መቅደሱን ያረክሳሉ፣
በሕግም ላይ ያምፃሉ።
5በርሷ ውስጥ ያለው እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤
ፈጽሞ አይሳሳትም፤
በየማለዳው ቅን ፍርድ ይሰጣል፤
በየቀኑም አይደክምም፤
ዐመፀኞች ግን ዕፍረት አያውቁም።
6“ሕዝቦችን አጥፍቻለሁ፤
ምሽጋቸው ተደምስሷል፤
ማንም እንዳያልፍባቸው፣
መንገዳቸውን ባድማ አደረግሁ፤
ከተሞቻቸው ተደምስሰዋል፤
አንድም ሰው የለም፤ ነዋሪም ከቶ አይገኝባቸውም።
7እኔም ከተማዪቱን፣
‘በርግጥ ትፈሪኛለሽ፤
ዕርምትም ትቀበያለሽ’ አልኋት፤
ስለዚህ መኖሪያዋ አይጠፋም፤
ቅጣቴም ሁሉ በርሷ ላይ አይደርስም።
እነርሱ ግን በሚያደርጉት ሁሉ፣
ክፋትንም በመፈጸም እየተጉ ሄዱ።”
8 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ስለዚህ እስከምፈርድበት#3፥8 የሰባ ሊቃናቱና የሱርስቱ ቅጅ ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ የዕብራይስጡ ትርጕም ግን ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ይላል። ቀን ድረስ
ጠብቁኝ፤
አሕዛብን ላከማች፣
መንግሥታትን ልሰበስብ፣
መዓቴንና ጽኑ ቍጣዬን
በላያቸው ላፈስስ ወስኛለሁ።
በቅናቴ ቍጣ እሳት፣
መላዋ ምድር ትቃጠላለችና።
9“በዚያ ጊዜ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም እንዲጠሩ፣
ተስማምተው እንዲያገለግሉት፣
አንደበታቸውን አጠራለሁ።
10ከኢትዮጵያ#3፥10 ይህ ከአባይ ወንዝ በስተሰሜን የሚገኝ አካባቢ ነው። ወንዞች ማዶ፣
የሚያመልኩኝ፣ የተበተኑት ሕዝቤ
ቍርባን ያመጡልኛል።
11በእኔ ላይ ከፈጸማችሁት በደል ሁሉ የተነሣ፣
በዚያ ቀን አታፍሩም፤
በትዕቢታቸው የሚደሰቱትን፣
ከዚህች ከተማ አስወግዳለሁና፤
ከእንግዲህ ወዲያ፣
በቅዱስ ተራራዬ ላይ አትታበዩብኝም።
12እግዚአብሔር ስም የሚታመኑትን፣
የዋሃንንና ትሑታንን፣
በመካከላችሁ አስቀራለሁ።
13የእስራኤል ቅሬታዎች ኀጢአት አይሠሩም፤
ሐሰትም አይናገሩም፤
በአንደበታቸውም ተንኰል አይገኝም።
ይበላሉ፤ ይተኛሉ፤
የሚያስፈራቸውም የለም።”
14የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ዘምሪ፤
እስራኤል ሆይ፤ እልል በዪ፤
የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤
በፍጹም ልብሽ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ።
15 እግዚአብሔር ቅጣትሽን አስወግዶታል፤
ጠላቶችሽን ከአንቺ መልሷል፤
የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው፤
ከእንግዲህ ወዲያ አንዳች ክፉ ነገር አትፈሪም።
16በዚያ ቀን ኢየሩሳሌምን እንዲህ
ይሏታል፤
“ጽዮን ሆይ፤ አትፍሪ፤
እጆችሽም አይዛሉ።
17 እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤
እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤
በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤
በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤
በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።”
18“ስለ ክብረ በዓላት መተጓጐል የተከዝሽበትን፣
የስድብሽን ሸክም፤
ከአንቺ አስወግዳለሁ።#3፥18 ወይም ስለ ክብረ በዓላት መተጓጐል የሚተክዙትን፣ የስድብ ሸክም የተከመረባቸውን መልሼ እሰበስባለሁ።
19በዚያ ጊዜ፣
ያስጨነቁሽን ሁሉ እቀጣለሁ፤
ዐንካሶችን እታደጋለሁ፤
የተበተኑትንም እሰበስባለሁ፤
በተዋረዱበት ምድር ሁሉ፣
ለውዳሴና ለክብር አደርጋቸዋለሁ።
20በዚያ ጊዜ እሰበስባችኋለሁ፤
ያን ጊዜ ወደ አገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤
ዐይናችሁ እያየ፣
ምርኳችሁን በምመልስበት ጊዜ፣
መከበርንና መወደስን፣
በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ”፤
ይላል እግዚአብሔር

Currently Selected:

ሶፎንያስ 3: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ