ዘካርያስ 7
7
ፍትሕና ምሕረት የተወደደ ነው
1ዳርዮስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ካሴሉ በተባለው በዘጠነኛው ወር፣ በአራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 2የቤቴል ሰዎች እግዚአብሔርን ለመለመን ሳራሳርንና ሬጌሜሌክን ዐብረዋቸው ከነበሩት ሰዎች ጋራ ላኩ፤ 3እነርሱም የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቤት ካህናትና ነቢያት፣ “ብዙ ዓመት እንዳደረግሁት፣ በዐምስተኛው ወር ማዘንና መጾም ይገባኛልን?” ብለው ጠየቁ።
4ከዚያም የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 5“የምድሩን ሕዝብ ሁሉና ካህናቱን እንዲህ በላቸው፤ ‘ባለፉት ሰባ ዓመታት በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር የጾማችሁትና ያዘናችሁት በርግጥ ለእኔ ነበርን? 6ትበሉና ትጠጡ የነበረውስ ለራሳችሁ አይደለምን? 7ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች በሰላምና በብልጽግና ላይ ሳሉ፣ የደቡብና የምዕራብ ኰረብቶች ግርጌ የሰው መኖሪያም በነበሩበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት የተናገረው ቃል ይህ አልነበረምን?’ ”
8የእግዚአብሔር ቃል እንደ ገና ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 9“የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እውነተኛ ፍትሕ አስፍኑ፣ እርስ በርሳችሁ ምሕረትና ርኅራኄን አድርጉ፤ 10መበለቲቱን ወይም ድኻ አደጉን፣ መጻተኛውን ወይም ድኻውን አታስጨንቁ፤ በልባችሁም አንዳችሁ በአንዳችሁ ላይ ክፉ አታስቡ።’
11“እነርሱ ግን ማስተዋል አልፈለጉም፤ በእልኸኝነት ጀርባቸውን አዞሩ፤ ጆሯቸውንም ደፈኑ። 12ልባቸውን እንደ አልማዝ አጠነከሩ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት በኩል በመንፈሱ የላከውን ቃል ወይም ሕግ አልሰሙም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ጸባኦት እጅግ ተቈጣ።
13“ ‘ስጠራቸው አልሰሙም፤ ስለዚህ ሲጠሩኝ አልሰማም’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 14‘በማያውቋቸው በባዕዳን አሕዛብ መካከል በዐውሎ ነፋስ በተንኋቸው፤ ከእነርሱ በኋላ ማንም እስከማይመጣባትና እስከማይሄድባት ድረስ ምድሪቱ ባድማ ሆነች፤ መልካሚቱን ምድር ባድማ ያደረጓት በዚህ ሁኔታ ነው።’ ”
Currently Selected:
ዘካርያስ 7: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.