ዘካርያስ 6
6
አራቱ ሠረገሎች
1እንደ ገናም ወደ ላይ ተመለከትሁ፤ እነሆ አራት ሠረገሎች ከሁለት ተራራ መካከል ሲወጡ አየሁ፤ ተራሮቹም የናስ ተራሮች ነበሩ። 2የመጀመሪያው ሠረገላ ቀይ ፈረስ፣ ሁለተኛው ጥቍር ፈረስ፤ 3ሦስተኛው ነጭ፣ አራተኛውም ዝጕርጕር ፈረሶች ነበሯቸው፤ ሁሉም ጠንካሮች ነበሩ። 4እኔም፣ ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረውን መልአክ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁት።
5መልአኩም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ አራቱ ቆመው ከነበሩበት ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት የወጡ የሰማይ መናፍስት#6፥5 ወይም ነፋሳት ሊሆን ይችላል። ናቸው። 6የባለ ጥቍር ፈረሶች ወደ ሰሜን፤ የባለ ነጭ ፈረሶች ወደ ምዕራብ#6፥6 ወይም ከኋላቸው ፈረሶች እንደ ማለት ነው። አገር፣ የባለዝጕርጕር ፈረሶች ወደ ደቡብ አገር ይወጣል።”
7ጠንካሮቹ ፈረሶች ሲወጡ፣ በምድር ሁሉ ለመመላለስ አቈብቍበው ነበር። እርሱም፣ “ወደ ምድር ሁሉ ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ሄዱ።
8ከዚያም ጮኾ እንዲህ አለኝ፤ “እነሆ፤ ወደ ሰሜን አገር የሚወጡት፣ መንፈሴን በሰሜን ምድር አሳርፈውታል።”
ለኢያሱ የተደረገለት አክሊል
9ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 10“ከባቢሎን ከመጡት ምርኮኞች ከሔልዳይና ከጦብያ፣ ከዮዳኤም ወርቅና ብር ውሰድ፤ በዚያው ቀን ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ሂድ። 11ወርቁንና ብሩን ወስደህ አክሊል ሥራ፤ በኢዮሴዴቅ ልጅ በሊቀ ካህኑ በኢያሱ ራስ ላይም አድርገው፤ 12ለርሱም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፤ ‘እነሆ፤ ስሙ ቅርንጫፍ የተባለው ሰው ይህ ነው፤ እርሱም በቦታው ይንሰራፋል፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ይሠራል። 13የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚሠራው እርሱ ነው፤ ክብርን ይጐናጸፋል፤ በዙፋኑ ተቀምጦ ይገዛል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፤ በሁለቱም መካከል የሰላም ምክር ይኖራል።’ 14አክሊሉም ለሔሌምና#6፥14 ሲርያክ፤ ዕብራይስጡ ሔሌም ይላል። ለጦብያ፣ ለዮዳኤና ለሶፎንያስ ልጅ ለሔን#6፥14 ወይም ርኅሩኁ እንደ ማለት ነው። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ መታሰቢያ ይሆናል። 15እነዚያ በሩቅ ያሉት መጥተው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሲሠራ ያግዛሉ፤ እናንተም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር በጥንቃቄ ብትታዘዙ ይህ ይሆናል።”
Currently Selected:
ዘካርያስ 6: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.