የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘካርያስ 11

11
1ሊባኖስ ሆይ፤ እሳት ዝግባሽን እንዲበላው
ደጆችሽን ክፈቺ!
2የጥድ ዛፍ ሆይ፤ ዝግባ ወድቋልና አልቅስ፤
የከበሩትም ዛፎች ጠፍተዋል!
የባሳን ወርካዎች ሆይ፤ አልቅሱ፤
ጥቅጥቅ ያለው ደን ተመንጥሯል!
3የእረኞችን ዋይታ ስሙ፤
ክብራቸው ተገፍፏልና፤
የአንበሶችን ጩኸት ስሙ፤
ጥቅጥቅ ያለው የዮርዳኖስ ደን ወድሟል!
ሁለቱ እረኞች
4 እግዚአብሔር አምላኬ እንዲህ ይላል፤ “ለዕርድ የተለዩትን በጎች አሰማራ፤ 5የገዟቸው ያርዷቸዋል፤ ሳይቀጡም ይቀራሉ፤ የሸጧቸውም፣ ‘እግዚአብሔር ይመስገን፤ ባለጠጋ ሆኛለሁ’ ይላሉ፤ ጠባቂዎቻቸውም እንኳ አይራሩላቸውም። 6ከእንግዲህ በምድሪቱ ለሚኖረው ሕዝብ አልራራምና” ይላል እግዚአብሔር፤ “ሰውን ሁሉ ለባልንጀራውና ለንጉሡ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱ ምድሪቱን ያስጨንቃሉ፤ እኔም ከእጃቸው አላድናቸውም።”
7ስለዚህ ለዕርድ የተለዩትን በጎች፣ በተለይም የተጨቈኑትን አሰማራሁ። ሁለት በትሮች ወስጄም፣ አንዱን “ሞገስ” ሌላውንም “አንድነት” ብዬ ጠራኋቸው፤ መንጋውንም አሰማራሁ። 8በአንድ ወር ውስጥ ሦስቱን እረኞች አስወገድሁ።
በጎቹ ጠሉኝ፤ እኔም፣ ሰለቸኋቸው፤ 9“እረኛችሁ አልሆንም፤ የሚሞቱት ይሙቱ፤ የሚጠፉት ይጥፉ፤ የቀሩትም አንዱ የሌላውን ሥጋ ይብላ” አልኋቸው።
10ከዚያም ከአሕዛብ ሁሉ ጋራ የገባሁትን ኪዳን ለማፍረስ፣ “ሞገስ” ብዬ የጠራሁትን በትሬን ወስጄ ሰበርሁት። 11በዚያም ቀን ኪዳኑ ፈረሰ፤ ሲመለከቱኝ የነበሩትና የተጨነቁት በጎችም የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ዐወቁ።
12እኔም፣ “የሚበጅ መስሎ ከታያችሁ ዋጋዬን ክፈሉኝ፤ አይሆንም ካላችሁም ተዉት” አልኋቸው፤ ስለዚህ ሠላሳ ብር ከፈሉኝ።
13 እግዚአብሔርም ሊከፍሉኝ የተስማሙበትን ጥሩ ዋጋ “በግምጃ ቤቱ ውስጥ አኑረው” አለኝ፤ እኔም ሠላሳውን ብር ወስጄ በእግዚአብሔር ቤት ባለው ግምጃ ቤት አስቀመጥሁት።
14ከዚያም የእስራኤልንና የይሁዳን ወንድማማችነት በማፍረስ፣ “አንድነት” ብዬ የጠራሁትን ሁለተኛውን በትሬን ሰበርሁት።
15 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “እንደ ገና የቂል እረኛ ዕቃ ውሰድ፤ 16እነሆ፤ በምድሪቱ ላይ እረኛ አስነሣለሁ፤ እርሱም የጠፋውን አያስብም፤ የባዘነውን አይፈልግም፤ የተሰበረውን አይጠግንም፤ የዳነውንም አይቀልብም፤ ነገር ግን የሠባውን ሥጋ ይበላል፤ ሰኰናውንም ሳይቀር ይቀለጣጥማል።
17“መንጋውን ለሚተው፣
ለማይረባ እረኛ ወዮለት!
ሰይፍ ክንዱንና ቀኝ ዐይኑን ትውጋው!
ክንዱ ፈጽማ ትስለል!
ቀኝ ዐይኑም ጨርሳ ትታወር!”

Currently Selected:

ዘካርያስ 11: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ