የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሮሜ 2:1-16

ሮሜ 2:1-16 NASV

ስለዚህ አንተ በሌላው ላይ የምትፈርድ፣ የምታመካኝበት የለህም፤ በሌላው ላይ በምትፈርድበት ነገር ሁሉ፣ ራስህን ትኰንናለህ፤ ፈራጅ የሆንኸው አንተ ያንኑ ታደርጋለህና። እንደዚህ በሚያደርጉትም ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ ትክክለኛ መሆኑን እናውቃለን። እንግዲህ አንተ ሰው በሌሎች ላይ እየፈረድህ ያንኑ የምታደርግ ከሆነ፣ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃል? ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ የሚመራህ መሆኑን ሳትገነዘብ፣ የቸርነቱን፣ የቻይነቱንና የትዕግሥቱን ባለጠግነት ትንቃለህ? ነገር ግን በድንዳኔህና ንስሓ በማይገባ ልብህ ምክንያት ትክክለኛ ፍርዱ ሲገለጥ በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን በራስህ ላይ ቍጣን ታከማቻለህ። እግዚአብሔር “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል”። በጎ የሆነውን ጸንቶ በማድረግ ክብርን፣ ሞገስንና ዘላለማዊነትን ለሚሹ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። ነገር ግን በራስ ወዳዶች፣ እውነትን ትተው ክፋትን በሚከተሉ ፍርድና ቍጣ ይደርስባቸዋል። ክፉ በሚያደርግ በማንኛውም ሰው፣ አስቀድሞ በአይሁድ ከዚያም በአሕዛብ ላይ መከራና ጭንቀት ይሆናል፤ ነገር ግን በጎ ለሚሠራ ለማንኛውም፣ አስቀድሞ ለአይሁድ ከዚያም ለአሕዛብ ክብር፣ ሞገስና ሰላም ይሆንለታል፤ እግዚአብሔር ለማንም አያደላምና። ሕግ ሳይኖራቸው ኀጢአት የሠሩ ሁሉ ያለ ሕግ ይጠፋሉ፤ ሕግ እያላቸው ኀጢአት የሠሩ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን የሚባሉት ለሕጉ የሚታዘዙ እንጂ፣ ሕጉን የሚሰሙ አይደሉም። ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ሕግ የሚያዝዘውን ነገር በተፈጥሮ ሲያደርጉ፣ ሕግ ባይኖራቸውም እነርሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸው። ኅሊናቸው ስለሚመሰክር፣ ሐሳባቸው ስለሚከስሳቸው፣ ደግሞም ስለሚከላከልላቸው የሕግ ትእዛዝ በልባቸው የተጻፈ መሆኑን ያሳያሉ። ይህም በወንጌል እንደማስተምረው እግዚአብሔር በሰው ልብ የተሰወረውን በክርስቶስ በኩል በሚፈርድበት ዕለት ግልጽ ይሆናል።