እንግዲህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ተዋቸውን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ ከቶ አይሆንም! እኔ ራሴ ከብንያም ነገድ፣ የአብርሃም ዘር የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝ። እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝብ አልጣላቸውም። ኤልያስ በእስራኤል ላይ ክስ ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንዳቀረበ፣ መጽሐፍ ስለ እርሱ ምን እንደሚል አታውቁምን? “ጌታ ሆይ፤ ነቢያትህን ገድለዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ እኔም ብቻዬን ቀረሁ፤ ሊገድሉኝም ይፈልጋሉ።” እግዚአብሔር የሰጠው መልስ ግን ምን ነበር? “ጕልበታቸው ለበኣል ያልተንበረከከውን ሰባት ሺሕ ሰዎች ለራሴ አስቀርቻለሁ።” በአሁኑ ጊዜም እንደዚሁ በጸጋ የተመረጡ ቅሬታዎች አሉ። እንግዲህ በጸጋ ከሆነ በሥራ አይደለም፤ በሥራ ቢሆንማ ኖሮ ጸጋ፣ ጸጋ መሆኑ በቀረ ነበር። እንግዲህ ምንድን ነው? እስራኤል አጥብቀው የፈለጉትን አላገኙትም፤ የተመረጡት ግን አገኙት፤ የቀሩትም ልባቸው ደነደነ፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ “ዐይናቸው እንዳያይ፣ ጆሯቸውም እንዳይሰማ፣ እግዚአብሔር እስከዚህ ቀን ድረስ፣ የድንዛዜ መንፈስ ሰጣቸው።” ዳዊትም አለ፤ “ማእዳቸው ወጥመድና ማሰናከያ፣ ዕንቅፋትና ቅጣት ይሁንባቸው። ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፤ ወገባቸውም ለዘላለም ይጕበጥ።” ተመልሰው እስከማይድኑ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እንደ ገና እጠይቃለሁ፤ ከቶ አይሆንም! ይልቁንም እስራኤልን ለማስቀናት ሲባል በእነርሱ መተላለፍ ምክንያት ድነት ለአሕዛብ መጥቷል። ነገር ግን የእነርሱ መተላለፍ ለዓለም በረከት ከሆነ፣ ውድቀታቸውም ለአሕዛብ በረከት ከሆነ፣ ሙላታቸው ምን ያህል ታላቅ በረከት ያመጣ ይሆን? አሕዛብ ሆይ፤ ለእናንተ እናገራለሁ፤ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን አገልግሎቴን በትጋት እፈጽማለሁ፤ ይኸውም የገዛ ወገኖቼን እንዲቀኑ አነሣሥቼ ከእነርሱ ጥቂቱን ለማዳን ተስፋ በማድረግ ነው። የእነርሱ መተው ለዓለም ዕርቅን ካስገኘ፣ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት መነሣት ነው ከማለት በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? በኵር ሆኖ የቀረበው የቡሖው ክፍል ቅዱስ ከሆነ፣ ቡሖው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩ ቅዱስ ከሆነ፣ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸው። ከቅርንጫፎቹ አንዳንዶቹ ቢሰበሩ፣ አንተም የበረሓ ወይራ ሆነህ ሳለ በሌሎቹ መካከል ገብተህ ከተጣበቅህና ከወይራው ዘይት ሥር የሚገኘውን በረከት ተካፋይ ከሆንህ፣ በእነዚያ ቅርንጫፎች ላይ አትኵራራ። ብትኰራ ግን ይህን አስተውል፤ አንተ ሥሩን አትሸከምም፤ ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ። እንግዲህ፣ “ቅርንጫፎች የተሰበሩት እኔ እንድገባ ነው” ትል ይሆናል። ትክክል ነው፤ እነርሱ የተሰበሩት ካለማመን የተነሣ ነው፤ አንተም በእምነት ቆመሃል፤ ፍራ እንጂ ትዕቢተኛ አትሁን። እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራላቸው፣ ለአንተም አይራራልህምና።
ሮሜ 11 ያንብቡ
ያዳምጡ ሮሜ 11
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሮሜ 11:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች