መዝሙር 88
88
መዝሙር 88
ሰቈቃ
ማሕሌት፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር፤ ለመዘምራን አለቃ፤ በማኸላት የሚዘመር፤ የይዝራኤላዊው የኤማን ትምህርት።
1አዳኜ የሆንህ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤
በቀንና በሌሊት በፊትህ እጮኻለሁ።
2ጸሎቴ በፊትህ ትድረስ፤
ጆሮህንም ወደ ጩኸቴ አዘንብል፤
3ነፍሴ በመከራ ተሞልታለችና፤
ሕይወቴም ወደ ሲኦል#88፥3 መቃብር የሚሉ አሉ። ተቃርባለች።
4ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋር ተቈጠርሁ፤
ዐቅምም ዐጣሁ።
5በሙታን መካከል እንደ ተጣሉ፣
ተገድለው በመቃብር ውስጥ እንደ ተጋደሙ፣
አንተ ከእንግዲህ እንደማታስባቸው፣
ከእጅህም ወጥተው እንደ ተወገዱ ሆንሁ።
6በዐዘቅት ጥልቀት ውስጥ ጣልኸኝ፤
በጨለማ ጕድጓድ ውስጥ ከተትኸኝ።
7የቍጣህ ክብደት በላዬ ዐርፏል፤
በማዕበልህም ሁሉ አጥለቅልቀኸኛል። ሴላ
8የሚቀርቡኝ ባልንጀሮቼን ከእኔ አራቅህ፤
እንዲጸየፉኝም አደረግህ፤
ተከብቤአለሁ፤ ማምለጥም አልችልም፤
9ዐይኖቼም በሐዘን ፈዘዙ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ዘወትር ወደ አንተ እጣራለሁ፤
እጆቼንም ወደ አንተ ዘረጋሁ።
10ድንቅ ሥራህን ለሙታን ታሳያለህን?
የሙታንስ መናፍስት ተነሥተው ያመሰግኑሃልን? ሴላ
11ምሕረትህ በመቃብር ውስጥ፣
ታማኝነትህስ እንጦርጦስ#88፥11 በዕብራይስጥ አባዶን ማለት ነው፤ የመውደሚያ ስፍራ ነው። ይነገራልን?
12ድንቅ ሥራህ በጨለማ ስፍራ፣
ጽድቅህስ በመረሳት ምድር ትታወቃለችን?
13 እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን ትረዳኝ ዘንድ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤
በጧትም ጸሎቴን በፊትህ አደርሳለሁ።
14 እግዚአብሔር ሆይ፤ ለምን ታርቀኛለህ?
ፊትህንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለህ?
15እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ችግረኛና ለሞት የተቃረብሁ ነበርሁ፤
መዓትህ አሠቃየኝ፤ ግራም ተጋባሁ።
16ቍጣህ በላዬ ላይ ተከነበለ፤
መዓትህም አጠፋኝ።
17ቀኑን ሙሉ እንደ ጐርፍ ከበቡኝ፤
በአንድነትም ዙሪያዬን ዐጥረው ያዙኝ።
18ወዳጄንና ባልንጀራዬን ከእኔ አራቅህ፤
ጓደኛዬ ጨለማ ብቻ ሆኖ ቀረ።
Currently Selected:
መዝሙር 88: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.