መዝሙር 119:121-136

መዝሙር 119:121-136 NASV

ፍትሕና ጽድቅ ያለበትን ሠርቻለሁ፤ ለሚጨቍኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ። ለባሪያህ በጎነት ዋስትና ሁን፤ እብሪተኞች እንዲጨቍኑኝ አትፍቀድላቸው። ዐይኖቼ ማዳንህን፣ የጽድቅ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ። ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ መጠን አድርግ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ። እኔ ባሪያህ ነኝ፤ ምስክርነትህን ዐውቅ ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕግህ እየተጣሰ ነውና፣ ጊዜው አንተ የምትሠራበት ነው። ስለዚህ ከወርቅ፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ፣ ትእዛዞችህን ወደድሁ። መመሪያህ ሙሉ በሙሉ ልክ ነው አልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ። ምስክርነትህ ሁሉ ድንቅ ነው፤ ስለዚህ ነፍሴ ትጠብቀዋለች። የቃልህ ትርጓሜ ያበራል፤ አላዋቂዎችንም አስተዋዮች ያደርጋል። ትእዛዝህን ናፍቄአለሁና፣ አፌን ከፈትሁ፤ አለከለክሁም። ስምህን ለሚወድዱ ማድረግ ልማድህ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ወደ እኔ ተመልሰህ ምሕረት አድርግልኝ። አካሄዴን እንደ ቃልህ ቀና አድርግልኝ፤ ኀጢአትም በላዬ እንዲሠለጥን አትፍቀድ። ትእዛዝህን መጠበቅ እንድችል፣ ከሰዎች ጥቃት ታደገኝ። በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፤ ሥርዐትህንም አስተምረኝ። ሕግህ ባለመከበሩ፤ እንባዬ እንደ ውሃ ይፈስሳል።