አንዳንዶቹ በመርከብ ወደ ባሕር ወረዱ፤ በታላቅም ውሃ ላይ ሥራቸውን አከናወኑ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ በዚያ አዩ፤ ድንቅ አድራጎቱንም በጥልቁ ውስጥ ተመለከቱ። እርሱ ተናግሮ ዐውሎ ነፋስን አስነሣ፤ ነፋሱም ማዕበሉን ከፍ ከፍ አደረገ። ወደ ሰማይ ወጡ፤ ወደ ጥልቅም ወረዱ፤ ከመከራቸውም የተነሣ ሐሞታቸው ፈሰሰ። እንደ ሰከረ ሰው ዞሮባቸው ወዲያ ወዲህ ተንገዳገዱ፤ መላው ጠፍቶባቸው የሚያደርጉትን ዐጡ። በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። ዐውሎ ነፋሱን ጸጥ አደረገ፤ የባሕሩም ሞገድ ረጭ አለ። ጸጥ በማለቱም ደስ አላቸው፤ ወዳሰቡትም ወደብ አደረሳቸው። እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣ ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤ በሕዝብ ጉባኤ መካከል ከፍ ከፍ ያድርጉት፤ በሽማግሌዎችም ሸንጎ ይወድሱት። ወንዞችን ወደ ምድረ በዳ፣ የውሃ ምንጮችንም ወደ ደረቅ ምድር ለወጠ። ከነዋሪዎቿ ክፋት የተነሣ፣ ፍሬያማዋን ምድር በጨው የተበከለች አደረጋት። ምድረ በዳውን ወደ ውሃ መከማቻ፣ ደረቁንም ምድር ወደ ውሃ ምንጭ ቀየረ። የተራቡትን በዚያ አስቀመጠ፤ የሚኖሩባትንም ከተማ ሠሩ። በዕርሻውም ዘሩበት፤ ወይንም ተከሉ፤ ብዙ ፍሬም አመረቱ። ይባርካቸዋል፤ እነርሱም እጅግ ይበዛሉ፤ የከብቶቻቸውም ብዛት እንዲያንስ አያደርግም። በጭንቅ፣ በመከራና በሐዘን፣ ቍጥራቸው አንሶ፣ ተዋርደው ነበር፤ በመኳንንቱም ላይ መናቅን አዘነበባቸው፤ መውጫ መግቢያው በማይታወቅ በረሓ ውስጥም አንከራተታቸው። ድኾችን ግን ከጭንቀታቸው መዝዞ አወጣቸው፤ ቤተ ሰባቸውንም እንደ በግ መንጋ አበዛ። ልበ ቅኖች ይህን አይተው ሐሤት ያደርጋሉ፤ ጥመትም ሁሉ አፏን ትዘጋለች። እንግዲህ ማንም ብልኅ ቢሆን፣ ይህን ነገር ልብ ይበል፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።
መዝሙር 107 ያንብቡ
ያዳምጡ መዝሙር 107
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መዝሙር 107:23-43
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos