ዘኍልቍ 32:20-42

ዘኍልቍ 32:20-42 NASV

ከዚያም ሙሴ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ብታደርጉ ማለትም በእግዚአብሔር ፊት ታጥቃችሁ ለጦርነት ብትዘጋጁ፣ እንዲሁም ጠላቶቹን ከፊቱ አሳድዶ እስኪያስወጣ ድረስ ሁላችሁም በእግዚአብሔር ፊት ለጦርነት ዝግጁ ሆናችሁ ዮርዳኖስን ብትሻገሩ፣ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር ከተገዛች በኋላ ልትመለሱ ትችላላችሁ፤ ለእግዚአብሔርና ለእስራኤል ካለባችሁም ግዴታ ነጻ ትሆናላችሁ፤ ይህችም ምድር በእግዚአብሔር ፊት ርስታችሁ ትሆናለች። “ይህን ባታደርጉ ግን እግዚአብሔርን ትበድላላችሁ፤ ኀጢአታችሁ እንደሚያገኛችሁም ዕወቁ። ለሴቶቻችሁና ለልጆቻችሁ ከተሞች፣ ለበግና ለፍየል መንጎቻችሁም ጕረኖች ሥሩላቸው፤ የገባችሁበትን የተስፋ ቃል ግን ፈጽሙ።” የጋድና የሮቤል ሰዎች ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “እኛ አገልጋዮችህ ጌታችን ያዘዘንን እንፈጽማለን። ልጆቻችንና ሚስቶቻችን፣ የበግና የፍየል እንዲሁም የከብት መንጎቻችን እዚሁ በገለዓድ ከተሞች ይቀራሉ፤ ባሮችህ ግን ልክ ጌታችን እንዳለው እያንዳንዱ ሰው ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ለመዋጋት እንሻገራለን።” ከዚያም ሙሴ ለካህኑ ለአልዓዛር፣ ለነዌ ልጅ ለኢያሱና ለእስራኤል ነገድ ቤተ ሰብ አለቆች እነርሱን አስመልክቶ ትእዛዝ ሰጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “የጋድና የሮቤል ወንድ ሁሉ፣ እያንዳንዱ ለጦርነት በመዘጋጀት በእግዚአብሔር ፊት ከእናንተ ጋራ ዮርዳኖስን የሚሻገር ከሆነ፣ ምድሪቱም በእጃችሁ ስትገባ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ስጧቸው። ለጦርነት ተዘጋጅተው ከእናንተ ጋራ ካልተሻገሩ ግን፣ ርስታቸውን ዐብረዋችሁ በከነዓን መካፈል አለባቸው።” የጋድና የሮቤል ሰዎች እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ባሪያዎችህ እግዚአብሔር ያለውን ያደርጋሉ፤ ለጦርነት ዝግጁ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት ወደ ከነዓን እንሻገራለን፤ የምንወርሰው ርስት ግን ከዮርዳኖስ ወዲህ እዚሁ ይሆናል።” ከዚያም ሙሴ፣ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛትና የባሳንን ንጉሥ የዐግን ግዛት፣ ማለትም ምድሪቱንና ከነከተሞቿ በዙሪያዋ ያለውን ግዛት በሙሉ ለጋድና ለሮቤል ነገዶች እንዲሁም ለዮሴፍ ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጣቸው። የጋድ ልጆች፤ ዲቦንን፣ አጣሮትን፣ አሮዔርን፣ ዓጥሮትሾፋንን፣ ኢያዜርን፣ ዮግብሃን፣ ቤትኒምራንና ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሯቸው፤ እንዲሁም ለበግና ለፍየል መንጎቻቸው ጕረኖዎች አበጁላቸው። የሮቤልም ልጆች ሐሴቦንን፣ ኤልያሊንና ቂርያታይምን እንዲሁም ስማቸው የተለወጠውን ናባውን፣ በኣልሜዎንን፣ ሴባማንን ዐደሱ፤ ላደሷቸውም ከተሞች ስም አወጡላቸው። የምናሴ ልጅ የሆነው የማኪር ዘሮች ወደ ገለዓድ ሄደው ምድሪቱን በመያዝ፣ እዚያ የነበሩትን አሞራውያን አሳደዷቸው፤ ስለዚህ ሙሴ ገለዓድን የምናሴ ዘሮች ለሆኑት ለማኪራውያን ሰጣቸው፤ እነርሱም መኖሪያቸውን በዚያው አደረጉ። ከምናሴ ነገድ የሆነው ኢያዕር መኖሪያቸውን ወስዶ፣ የኢያዕር መንደሮች ብሎ ሰየማቸው። እንዲሁም ኖባህ ቄናትንና በዙሪያዋ ያሉትን መንደሮች በመያዝ በራሱ ስም፣ ኖባህ ብሎ ጠራቸው።