ዘኍልቍ 1
1
የሕዝብ ቈጠራ
1እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን በሲና ምድረ በዳ ሳሉ እግዚአብሔር ሙሴን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ተናገረው፤ እንዲህም አለው፤ 2“የወንዶቹን ስም አንድ በአንድ በመዘርዘር መላውን የእስራኤል ማኅበረ ሰብ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቍጠሯቸው። 3በመላው እስራኤል ያሉትን ዕድሜያቸው ሃያና ከዚያም በላይ ሆኖ ለውጊያ ብቁ የሆኑትን ወንዶች ሁሉ አንተና አሮን በየምድባቸው ቍጠሯቸው። 4ከየነገዱ የአባቶች ቤት ተጠሪ የሆነ አንድ ሰው ከእናንተ ጋራ ይሁን።
5“የሚረዷችሁም ሰዎች ስም የሚከተለው ነው፤
“ከሮቤል የስዲዮር ልጅ ኤሊሱር፤
6ከስምዖን የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል፤
7ከይሁዳ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን፤
8ከይሳኮር የሶገር ልጅ ናትናኤል፤
9ከዛብሎን የኬሎን ልጅ ኤልያብ፤
10ከዮሴፍ ልጆች ከኤፍሬም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ፤
ከምናሴ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል፤
11ከብንያም የጋዴዮን ልጅ አቢዳን፤
12ከዳን የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር፤
13ከአሴር የኤክራን ልጅ ፋግኤል፤
14ከጋድ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ፤
15ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አኪሬ።”
16እነዚህ ከማኅበረ ሰቡ የተመረጡ የየነገዱ አለቆች ሲሆኑ እነርሱም የእስራኤል ጐሣዎች መሪዎች ነበሩ።
17ሙሴና አሮን ስማቸው የተጠቀሰውን እነዚህን ሰዎች ወሰዱ፤ 18ከዚያም በሁለተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ማኅበረ ሰቡን በሙሉ በአንድነት ሰበሰቧቸው። የተሰበሰቡትም በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው የትውልድ ሐረጋቸውን ተናገሩ፤ 19እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆነ ወንዶች ስማቸው አንድ በአንድ ተመዘገበ። እንዲህ አድርጎም በሲና ምድረ በዳ ቈጠራቸው።
20ከእስራኤል የበኵር ልጅ ከሮቤል ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኖ በሰራዊቱ ውስጥ ለማገልገል ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ። 21ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩት አርባ ስድስት ሺሕ ዐምስት መቶ ነበሩ።
22ከስምዖን ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ። 23ከስምዖን ነገድ የተቈጠሩት ዐምሳ ዘጠኝ ሺሕ ሦስት መቶ ነበሩ።
24ከጋድ ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ። 25ከጋድ ነገድ የተቈጠሩትም አርባ ዐምስት ሺሕ ስድስት መቶ ዐምሳ ነበሩ።
26ከይሁዳ ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ። 27ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩትም ሰባ አራት ሺሕ ስድስት መቶ ነበሩ።
28ከይሳኮር ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ። 29ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩትም ዐምሳ አራት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ።
30ከዛብሎን ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ። 31ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩትም ዐምሳ ሰባት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ።
32ከዮሴፍ ልጆች፦
ከኤፍሬም ዝርያ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ። 33ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩትም አርባ ሺሕ ዐምስት መቶ ነበሩ።
34ከምናሴ ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ። 35ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩትም ሠላሳ ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ነበሩ።
36ከብንያም ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ፤ 37ከብንያም ነገድ የተቈጠሩትም ሠላሳ ዐምስት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ።
38ከዳን ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ። 39ከዳን ነገድ የተቈጠሩትም ስድሳ ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ ነበሩ።
40ከአሴር ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ። 41ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺሕ ዐምስት መቶ ነበሩ።
42ከንፍታሌም ዝርያ፦
ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት ወንዶች ሁሉ በየጐሣቸውና፣ በየቤተ ሰባቸው መዝገብ መሠረት ስማቸው አንድ በአንድ ተጻፈ። 43ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩትም ዐምሳ ሦስት ሺሕ አራት መቶ ነበሩ።
44በሙሴና በአሮን፣ እያንዳንዳቸውም ቤተ ሰባቸውን በወከሉት በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል አለቆች የተቈጠሩት ወንዶች እነዚህ ናቸው። 45ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ ሆኖ በእስራኤል ሰራዊት ውስጥ ለመዋጋት ብቁ የሆኑት በየቤተ ሰባቸው ተቈጠሩ፤ 46ጠቅላላ ቍጥራቸውም ስድስት መቶ ሦስት ሺሕ ዐምስት መቶ ዐምሳ ነበር።
47የሌዊ ነገድ ቤተ ሰቦች ግን ከሌሎች ጋራ ዐብረው አልተቈጠሩም፤ 48እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎት ነበርና፤ 49“የሌዊን ነገድ አትቍጠር፤ በእስራኤላውያንም ቈጠራ ውስጥ አታስገባው፤ 50በዚህ ፈንታ ሌዋውያንን በምስክሩ ማደሪያ፣ በውስጡ ባሉት በመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ እንዲሁም ከዚሁ ጋራ በተያያዙ በማናቸውም ነገሮች ላይ ኀላፊዎች ይሁኑ፤ ማደሪያውንና በውስጡ ያሉትን የመገልገያ ዕቃዎች ይሸከሙ፤ በውስጡ ያገልግሉ፤ ድንኳናቸውንም በዙሪያው ይትከሉ። 51ማደሪያው በሚነሣበት ጊዜ ሌዋውያን ይንቀሉት፤ ማደሪያው በሚተከልበትም ጊዜ ሌዋውያን ያቁሙት፤ ሌላ ሰው ቢቀርብ ግን ይገደል። 52እስራኤላውያን በየምድባቸው ድንኳናቸውን ይትከሉ፤ እያንዳንዱም ሰው በየሰፈሩና በየዐርማው ሥር ይስፈር። 53ሌዋውያን ግን በእስራኤላውያን ማኅበረ ሰብ ላይ ቍጣ እንዳይወርድ ድንኳኖቻቸውን በምስክሩ ማደሪያ ዙሪያ ይትከሉ፤ የምስክሩ ማደሪያ ድንኳን ኀላፊዎች ሌዋውያን ናቸው።”
54እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ይህን ሁሉ አደረጉ።
Currently Selected:
ዘኍልቍ 1: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.