ናሆም 1
1
1ስለ ነነዌ ጥፋት የተነገረ ንግር፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው፤
በነነዌ ላይ የተገለጠ የእግዚአብሔር ቍጣ
2 እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤
እግዚአብሔር የሚበቀል፣ በመዓትም የተሞላ ነው።
እግዚአብሔር ባላጋራዎቹን ይበቀላል፤
በጠላቶቹም ላይ ቍጣውን ያመጣል።
3 እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ በኀይሉም ታላቅ ነው፤
እግዚአብሔር በደለኛውን ሳይቀጣ አያልፍም፤
መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በማዕበል ውስጥ ነው፤
ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።
4ባሕርን ይገሥጻል፤ ያደርቀዋልም፤
ወንዞችን ሁሉ ያደርቃል።
ባሳንና ቀርሜሎስ ጠውልገዋል፤
የሊባኖስም አበቦች ረግፈዋል።
5ተራሮች በፊቱ ታወኩ፤
ኰረብቶችም ቀለጡ።
ምድር በፊቱ፣
ዓለምና በውስጧ የሚኖሩት ሁሉ ተናወጡ።
6ቍጣውን ማን ሊቋቋም ይችላል?
ጽኑ ቍጣውንስ ማን ሊሸከም ይችላል?
መዓቱ እንደ እሳት ፈስሷል፤
ዐለቶችም በፊቱ ተሰነጣጥቀዋል።
7 እግዚአብሔር መልካም ነው፤
በጭንቅ ጊዜም መሸሸጊያ ነው።
ለሚታመኑበት ይጠነቀቅላቸዋል፤
8ነነዌን ግን፣
በሚያጥለቀልቅ ጐርፍ ያጠፋታል፤
ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል።
9በእግዚአብሔር ላይ ምንም ቢያሤሩ#1፥9 በእግዚአብሔር ላይ የምታሤሩት ምንድን ነው? የሚሉ አሉ።፣
እርሱ ያጠፋዋል፤
መከራም ዳግመኛ አይነሣም።
10በእሾኽ ይጠላለፋሉ፤
በወይን ጠጃቸውም ይሰክራሉ፤
እሳትም እንደ ገለባ#1፥10 የዕብራይስጡ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። ይበላቸዋል።
11ነነዌ ሆይ፤ በእግዚአብሔር ላይ የሚያሤር፣
ምናምንቴ ክፉ መካሪ፣
ከአንቺ ዘንድ ወጥቷል።
12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ምንም ኀይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑም፣
ይቈረጣሉ፤ ይጠፋሉም።
ይሁዳ ሆይ፤ ከዚህ በፊት ባስጨንቅህም፣
ከእንግዲህ አላስጨንቅህም።
13አሁንም ቀንበራቸውን ከዐንገትህ ላይ አንሥቼ እሰብራለሁ፤
የታሰርህበትንም ሰንሰለት በጥሼ እጥላለሁ።”
14አንቺ ነነዌ፤ እግዚአብሔር ስለ አንቺ እንዲህ ብሎ አዝዟል፤
“ስም የሚያስጠራ ትውልድ አይኖራችሁም፤
በአማልክታችሁ ቤት ያሉትን፣
የተቀረጹትን ምስሎችና ቀልጠው የተሠሩትን ጣዖታት እደመስሳለሁ፤
መቀበሪያህን እምስልሃለሁ፤
አንተ ክፉ ነህና።”
15እነሆ፤ የምሥራች የሚያመጣው፣
ሰላምን የሚያውጀው ሰው እግር፣
በተራሮች ላይ ነው፤
ይሁዳ ሆይ፤ በዓላትህን አክብር፤
ስእለትህንም ፈጽም፤
ከእንግዲህ ምናምንቴ ሰዎች አይወርሩህም፤
እነርሱም ፈጽመው ይጠፋሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.