ማርቆስ 9:14-50

ማርቆስ 9:14-50 NASV

ወደ ቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ፣ ብዙ ሕዝብ ከብበዋቸው፣ የኦሪት ሕግ መምህራን ከእነርሱ ጋራ ሲከራከሩ አዩ። ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩት ወዲያው ተደንቀው እጅ ሊነሡት ወደ እርሱ ሮጡ። እርሱም፣ “ከእነርሱ ጋራ የምትከራከሩት ስለ ምን ጕዳይ ነበር” ሲል ጠየቃቸው። ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ ዐድሮበት ድዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ ዐረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፣ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋራ እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት።” አላቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፣ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፣ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።” ኢየሱስም፣ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፣ “አምናለሁ፤ አለማመኔን ርዳው!” በማለት ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ ወደዚያ እየተንጋጋ በሩጫ መምጣቱን ባየ ጊዜ፣ “አንተ ደንቈሮና ድዳ መንፈስ ከርሱ ውጣ! ከእንግዲህም ተመልሰህ እንዳትገባበት አዝዝሃለሁ” ብሎ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ እየጮኸ ክፉኛ ካንፈራገጠው በኋላ ከልጁ ወጣ፤ ብዙዎቹ “ሞቷል” እስኪሉ ድረስ ልጁ እንደ በድን ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ በእግሮቹ ቆመ። ወደ ቤት ከገባም በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ቀርበው፣ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “የዚህ ዐይነቱ ሊወጣ የሚችለው በጸሎትና በጾም ብቻ ነው” አላቸው። ከዚያም ተነሥተው በገሊላ በኩል ዐለፉ፤ ኢየሱስም ያሉበትን ስፍራ ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም፤ ለደቀ መዛሙርቱ፣ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ይነሣል” እያለ ያስተምራቸው ነበር። እነርሱ ግን የሚላቸው አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ። ከዚህ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ቤት ከገባ በኋላም፣ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለ ምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱ ግን በመንገድ ላይ የተከራከሩት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው በሚል ስለ ነበር ዝም አሉ። ከተቀመጠ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ፣ ከሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው። አንድ ሕፃን አምጥቶም በመካከላቸው አቆመ፤ ዐቅፎትም፣ “ከእነዚህ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበለኝ ማንም ቢኖር የሚቀበለው እኔን ሳይሆን የላከኝን ነው” አላቸው። ዮሐንስም፣ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየነው፣ እኛን ስለማይከተልም ልንከለክለው ሞከርን” አለው። ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “አትከልክሉት፤ ማንም በስሜ ታምር ሠርቶ ወዲያውኑ በእኔ ላይ ክፉ መናገር አይችልም፤ የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋራ ነውና፤ እውነት እላችኋለሁ፣ የክርስቶስ በመሆናችሁ በስሜ አንድ ኩባያ ውሃ የሚሰጣችሁ ሁሉ ዋጋውን አያጣም። “ማንም በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያሰናክል ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል። ስለዚህ እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ እሳቱ ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ከመሄድ፣ ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤ [በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና።] እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ ዐንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤ [በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና።] ዐይንህ ብታሰናክልህ ጐልጕለህ አውጣት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል፤ “ ‘በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና።’ ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና። “ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨው ጨውነቱን ቢያጣ እንዴት መልሳችሁ ጣዕም እንዲኖረው ታደርጉታላችሁ? ጨው በውስጣችሁ ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች