ማርቆስ 8:22-38

ማርቆስ 8:22-38 NASV

ከዚያም ወደ ቤተ ሳይዳ መጡ፤ ጥቂት ሰዎችም አንድ ዐይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ለመኑት። እርሱም የዐይነ ስውሩን እጅ ይዞ ከሰፈር ውጭ አወጣው፤ በዐይኖቹም ላይ እንትፍ ብሎበት፣ እጁንም በላዩ ጭኖ፣ “ምን የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም ቀና ብሎ አይቶ፣ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” አለ። ኢየሱስም እንደ ገና እጆቹን በሰውየው ዐይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ። ከዚያም፣ “ወደ መንደሩ አትግባ! በመንደሩም ለማንም አትናገር” ብሎ ወደ ቤቱ ሰደደው። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሰዎች እኔን ማን ነው ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት። ቀጥሎም፣ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ጴጥሮስም፣ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው። ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው። ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፣ እንደሚገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር። እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፣ “አንተ ሰይጣን፤ ወደ ኋላዬ ሂድ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ የለምና” በማለት ገሠጸው። ከዚህ በኋላ፣ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ለማዳን የሚወድድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። ሰው ዓለሙ ሁሉ የርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል? ለመሆኑ፣ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው? በዚህ ዘማዊና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅም በአባቱ ግርማ፣ ከቅዱሳን መላእክት ጋራ ሲመጣ ያፍርበታል።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች