የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 4:1-20

ማርቆስ 4:1-20 NASV

በሌላ ጊዜ ደግሞ በባሕሩ አጠገብ ያስተምር ጀመር። እርሱ ባለበት አካባቢ እጅግ ብዙ ሕዝብ ስለ ተሰበሰበ፣ በባሕሩ ላይ ወዳለች ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ባለው ስፍራ ላይ ተሰብስቦ ነበር። እርሱም ብዙ ነገሮችን በምሳሌ አስተማራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ስሙ፤ አንድ ዘሪ ዘር ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም ሳለ አንዳንዱ ዘር መንገድ ላይ ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። አንዳንዱም ዘር በቂ ዐፈር በሌለበት በድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ፈጥኖ በቀለ፤ ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ባለመስደዱም ደረቀ። ሌላው ዘር ደግሞ በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አድጎ የዘሩን ተክል ስላነቀው ፍሬ አላፈራም። ሌላውም ዘር ደግሞ በመልካም መሬት ላይ ስለ ወደቀ በቅሎ አደገ፤ ፍሬም ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፣ አንዱ ስድሳ፣ ሌላውም መቶ ፍሬ አፈራ።” ቀጥሎም ኢየሱስ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ። ብቻውን በሆነ ጊዜ፣ ዐሥራ ሁለቱና ዐብረውት የነበሩት ሌሎች ስለ ምሳሌዎቹ ጠየቁት። እርሱም፣ “ለእናንተ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ተሰጥቷችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን ነገር ሁሉ በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ ይኸውም፣ “ ‘ማየቱን እንዲያዩ እንዳያስተውሉትም፣ መስማቱን እንዲሰሙ ልብ እንዳይሉትም፣ እንዳይመለሱና ኀጢአታቸው እንዳይሰረይላቸው ነው’ አላቸው።” ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ምሳሌ አልተረዳችሁትምን? ታዲያ ሌሎቹን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? ዘሪው ቃሉን ይዘራል። አንዳንድ ሰዎች በመንገድ ላይ የወደቀውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ሰይጣን ወዲያውኑ መጥቶ በውስጣቸው የተዘራውን ቃል ይወስደዋል። እንዲሁም ሌሎች በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤ ነገር ግን ሥር ስላልሰደዱ፣ የሚቈዩት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያውኑ ይሰናከላሉ። ሌሎቹ ደግሞ በእሾኽ መካከል የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን መስማት ይሰማሉ፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ፣ የሀብት አጓጊነት እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ምኞት ቃሉን ዐንቀው በመያዝ ፍሬ እንዳያፈራ ያደርጉታል። ሌሎቹ በመልካም መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ እነዚህም ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉና ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች