ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። እነርሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸው፤ ገንዘብ ሊሰጡትም ቃል ገቡለት፤ ስለዚህ እርሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ የውሃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ የፋሲካን እራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?’ ብሏል በሉት፤ እርሱም በሰገነት ላይ ተነጥፎ የተሰናዳ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን።” ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ መጣ። በማእድ ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ፣ ዐብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው። እነርሱም ዐዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፣ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፣ ከእኔ ጋራ እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ግን ወዮለት! ያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።” ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፣ “ዕንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው። ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ። ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ከወይን ፍሬ አልጠጣም።” ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ’ ከተነሣሁ በኋላ ግን፣ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም፣ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አልሰናከልም” አለ። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም፣ “ከአንተ ጋራ ብሞት እንኳ ከቶ አልክድህም” በማለት ይበልጥ አጽንቶ ተናገረ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ።
ማርቆስ 14 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 14
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 14:10-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች