ከዚያም በነገር እንዲያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። እነርሱም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛ ሰው መሆንህን፣ ለማንም ሳታደላ ሁሉንም እኩል እንደምትመለከት እናውቃለን፤ ይልቁንስ የእግዚአብሔርን መንገድ ብቻ በእውነት ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም? እኛስ እንክፈል ወይስ አንክፈል?” ኢየሱስ ግን ግብዝነታቸውን ዐውቆ፣ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስኪ አንድ ዲናር አምጡልኝና ልየው” አላቸው። እነርሱም አመጡለት፣ “ይህ የማን መልክ ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው፤ እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” አሉት። ኢየሱስም፣ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በርሱ እጅግ ተደነቁ። ከዚህ በኋላ ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ የአንድ ሰው ወንድም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ወንድሙ የሟችን ሚስት አግብቶ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል። ታዲያ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው አግብቷት ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሁለተኛውም ሴትዮዋን አገባት፤ እርሱም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤ ሰባቱም አገቧት፤ ዘር ግን አልተኩም፤ በመጨረሻም ሴትዮዋ ሞተች። እንግዲህ፣ ሰባቱም አግብተዋታልና በትንሣኤ ለማንኛቸው ሚስት ልትሆን ነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ስለማታውቁ የምትስቱ አይደለምን? ሙታን በሚነሡበት ጊዜ እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም። ስለ ሙታን መነሣት ግን፣ በሙሴ መጽሐፍ ይኸውም ስለ ቍጥቋጦው በተነገረው ክፍል፣ እግዚአብሔር ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ያለውን አላነበባችሁምን? እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ስለዚህ እጅግ ተሳስታችኋል!” ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፣ “ለመሆኑ ከትእዛዞች ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን፣ ጌታ አንድ ነው። አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።” ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እግዚአብሔር አንድ መሆኑን፣ ከርሱም ሌላ አለመኖሩን እውነት ተናግረሃል፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።” ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ “ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ? ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፣ “ ‘ጌታ ጌታዬን፣ “ጠላቶችህን ከእግሮችህ በታች እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው። ይላል፤’ ታዲያ ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ካለው፣ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር። ሲያስተምርም እንዲህ አለ፤ ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ “ዘርፋፋ ቀሚስ ለብሰው መዞርን፣ በገበያ ስፍራ የአክብሮት ሰላምታን፣ በምኵራብ የከበሬታ መቀመጫን፣ በግብዣ ቦታም የክብር ስፍራን ይፈልጋሉና፤ በረዥም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቍታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።” ኢየሱስ በመባ መክተቻው ሣጥን ትይዩ ተቀምጦ፣ ብዙ ሰዎች ስጦታቸውን ሲያስገቡ ይመለከት ነበር። ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ አስገቡ፤ አንዲት ምስኪን መበለት ግን ከአንድ ሳንቲም የማይበልጡ ሁለት የናስ ሳንቲሞች አስገባች። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት ሙዳየ መባ ውስጥ ሌሎቹ ከጨመሩት የበለጠ አስገባች። እነዚህ ሁሉ ከተረፈው ሀብታቸው ሰጡ፤ እርሷ ግን ከጕድለቷ ያላትን፣ መኖሪያዋን ሁሉ ሰጠች።”
ማርቆስ 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 12:13-44
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች