ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፣ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጕልበቱ ተንበርክኮ፣ “መልካም መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር መልካም ማንም የለም፤ ‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አታታልል፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ትእዛዝ ታውቃለህ።” ሰውየውም፣ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው። ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ ሀብት ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው። ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ አዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው እየተከዘ ሄደ። ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ምንኛ ከባድ ነገር ነው!” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደ ገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ምንኛ ከባድ ነገር ነው! ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀልለዋል።” ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፣ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ። ኢየሱስም አያቸውና፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉም ነገር ይቻላል” አላቸው።
ማርቆስ 10 ያንብቡ
ያዳምጡ ማርቆስ 10
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማርቆስ 10:17-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos