ሚክያስ 6
6
የእግዚአብሔር ክስ በእስራኤል ላይ
1 እግዚአብሔር የሚለውን ስሙ፤
“ተነሡ፤ ጕዳያችሁን በተራሮች ፊት አቅርቡ፤
ኰረብቶች እናንተ የምትሉትን ይስሙ።
2“ተራሮች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ክስ አድምጡ፤
እናንተ የምድር ጽኑ መሠረቶችም፣ ስሙ፤
እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋራ ክርክር አለውና፤
ከእስራኤልም ጋራ ይፋረዳል።
3“ሕዝቤ ሆይ፤ ምን አድርጌሃለሁ?
ሸክም የሆንሁብህስ እንዴት ነው?
እስኪ መልስልኝ!
4ከግብጽ አወጣሁህ፤
ከባርነት ምድርም ተቤዠሁህ፤
እንዲመሩህ ሙሴን፣
አሮንንና ማርያምን ላክሁልህ።
5ሕዝቤ ሆይ፤
የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ የመከረውን፣
የቢዖር ልጅ በለዓም የመለሰለትንም እስኪ አስቡ፤
የእግዚአብሔርን የጽድቅ ሥራ ታውቁ ዘንድ፣
ከሰጢም እስከ ጌልገላ የተጓዛችሁትን ዐስቡ።”
6ምን ይዤ በእግዚአብሔር ፊት ልቅረብ፣
በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ?
የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣
ከአንድ ዓመት ጥጃ ጋራ ይዤ በፊቱ ልቅረብን?
7በአንድ ሺሕ አውራ በጎች፣
በዐሥር ሺሕ የዘይት ፈሳሽ እግዚአብሔር ደስ ይለዋልን?
ስለ በደሌ የበኵር ልጄን፣
ስለ ነፍሴም ኀጢአት የሆዴን ፍሬ ላቅርብለትን?
8ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤
እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው?
ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣
በአምላክህም ፊት በትሕትና#6፥8 ወይም በቅንነት ትራመድ ዘንድ አይደለምን?
የእስራኤል በደልና ቅጣት
9ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፤
ስሙ! እግዚአብሔር ከተማዪቱን እንዲህ እያለ ይጣራል፤
“በትሩን አስቡ፤ ያዘጋጀውም ማን እንደ ሆነ አስታውሱ#6፥9 የዚህ ስንኝ የዕብራይስጡ ትርጕም በርግጠኛነት አይታወቅም።።
10የክፋት ቤት ሆይ፤
በግፍ የተገኘ ሀብታችሁን፣
በሐሰተኛ መስፈሪያ የሰበሰባችሁትን አስጸያፊ ነገር እረሳዋለሁን?
11አባይ ሚዛን የያዘውን ሰው፣
ሐሰተኛ መመዘኛ በከረጢት የቋጠረውን ንጹሕ ላድርገውን?
12ባለጠጎቿ ግፈኞች፣
ሰዎቿ ሐሰተኞች ናቸው፤
ምላሳቸውም አታላይ ናት።
13ስለዚህ አንተን አጠፋሃለሁ#6፥13 ወይም ስለዚህ ሕመምተኛ አደርግሃለሁ እና አጠፋሃለሁ/ አጠፋሃለሁ።፣
ከኀጢአትህ የተነሣ አፈራርስሃለሁ።
14ትበላለህ፤ ነገር ግን አትጠግብም፤
ሆድህ እንዳለ ባዶውን#6፥14 የዚህ ቃል የዕብራይስጡ ትርጕም በርግጠኛነት አይታወቅም። ይቀራል፤
ታከማቻለህ፤ ነገር ግን አይጠራቀምልህም፤
የሰበሰብኸውን ለሰይፍ አደርገዋለሁና።
15ትዘራለህ፤ ነገር ግን አታጭድም፤
የወይራ ዘይት ትጨምቃለህ፤ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፤
ወይንን ትቈርጣለህ፤ ነገር ግን የወይን ጠጅ አትጠጣም።
16የዖምሪን ሥርዐት፣
የአክዓብን ቤት ልምድ ሁሉ የሙጥኝ ብለሃል፤
ትውፊታቸውንም ተከትለሃል።
ስለዚህ አንተን ለውድመት፣
ሕዝብህን ለመዘባበቻ አሳልፌ እሰጣለሁ፤
አሕዛብም ይሣለቁብሃል#6፥16 የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ከዚህ ጋራ ሲስማማ የዕብራይስጡ ግን የሕዝቤን ስድብ ትሸከማለህ ይላል።።”
Currently Selected:
ሚክያስ 6: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.