ሚክያስ 5
5
ከቤተ ልሔም ገዥ እንደሚመጣ የተሰጠ ተስፋ
1አንቺ የጭፍሮች ከተማ ሆይ፤
ጭፍሮችሽን አሰልፊ#5፥1 ወይም አንቺ የተቀጠርሽ ከተማ ሆይ፤ ቅጥርሽን አጥብቂ፤
ከበባ ተደርጎብናልና።
የእስራኤልን ገዥ፣
ጕንጩን በበትር ይመቱታል።
2“አንቺ ግን፣ ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፤
ከይሁዳ ነገዶች#5፥2 ወይም ገዦች መካከል ትንሿ ብትሆኚም፣
አመጣጡ ከጥንት፣#5፥2 ወይም ከቀድሞ ቀናት
ከቀድሞ ዘመን#5፥2 ዕብራይስጡ አወጣጡ ይላል ወይም ከዘላለም የሆነ የሆነ፣
የእስራኤል ገዥ፣
ከአንቺ ይወጣልኛል።”
3ስለዚህ ወላዲቱ አምጣ እስክትገላገል ድረስ፣
እስራኤል ትተዋለች፤
የተቀሩት ወንድሞቹም፣
ተመልሰው ከእስራኤላውያን ጋራ ይቀላቀላሉ።
4በእግዚአብሔር ኀይል፣
በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ታላቅነት፣
ጸንቶ ይቆማል፤ መንጋውንም ይጠብቃል።
በዚያ ጊዜ ኀያልነቱ እስከ ምድር ዳርቻ ስለሚደርስ፣
ተደላድለው ይኖራሉ።
5እርሱም ሰላማቸው ይሆናል።
ትድግናና ጥፋት
አሦራዊ ምድራችንን ሲወርር፣
ምሽጎቻችንንም ጥሶ ሲገባ፣
ሰባት እረኞችን፣
እንዲያውም ስምንት አለቆችን እናስነሣበታለን።
6የአሦርን ምድር በሰይፍ፣
የናምሩድን ምድር#5፥6 ወይም ናምሩድን በመግቢያው በር በተመዘዘ ሰይፍ ይገዛሉ#5፥6 ወይም ያፈርሳሉ፤
አሦራዊው ምድራችንን ሲወርር፣
ዳር ድንበራችንን ሲደፍር፣
እርሱ ነጻ ያወጣናል።
7የያዕቆብ ትሩፍ፣
በብዙ አሕዛብ መካከል
ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ ጠል፣
በሣር ላይ እንደሚጥል ካፊያ፣
ሰውን እንደማይጠብቅ፣
የሰውንም ልጆች ተስፋ እንደማያደርግ ሰው ይሆናል።
8በዱር አራዊት መካከል እንዳለ አንበሳ፣
በእግሩ እየጨፈላለቀ እንደሚሄድ፣
የሰበረውን ማንም ሊነጥቀው እንደማይችል፣
በበግ መንጋ መካከል እንዳለ፣
እንደ ደቦል አንበሳ ሁሉ፣
የያዕቆብም ትሩፍ፣ በአሕዛብ ዘንድ፣ በብዙም ሕዝብ መካከል እንደዚሁ ይሆናል።
9እጅህ በጠላቶችህ ላይ በድል አድራጊነት ከፍ ከፍ ትላለች፤
ጠላቶችህም ሁሉ ይጠፋሉ።
10“በዚያ ጊዜ” ይላል እግዚአብሔር፤
“ፈረሶቻችሁን ከመካከላችሁ አጠፋለሁ፤
ሠረገሎቻችሁን እደመስሳለሁ።
11የምድራችሁን ከተሞች እደመስሳለሁ፤
ምሽጎቻችሁንም ሁሉ አፈርሳለሁ።
12ጥንቈላችሁን አጠፋለሁ፤
ከእንግዲህም አታሟርቱም።
13የተቀረጹ ምስሎቻችሁን፣
የማምለኪያ ዐምዶቻችሁንም ከመካከላችሁ አጠፋለሁ፤
ከእንግዲህ ለእጃችሁ ሥራ
አትሰግዱም።
14የአሼራ ምስልን ዐምድ#5፥14 አሼራ የተባለችው አምላክ የዕንጨት ትእምርት ነው። ከመካከላችሁ እነቅላለሁ፤
ከተሞቻችሁንም እደመስሳለሁ።
15ያልታዘዙኝን አሕዛብ፣
በቍጣና በመዓት እበቀላቸዋለሁ።”
Currently Selected:
ሚክያስ 5: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.