ሚክያስ 4
4
የእግዚአብሔር ተራራ
1በመጨረሻው ዘመን፣
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ፣
ከተራሮችም ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤
ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ይላል፤
ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።
2ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤
“ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣
ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤
በጐዳናውም እንድንሄድ፣
መንገዱን ያስተምረናል።”
ሕግ ከጽዮን፤
የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።
3እርሱ በብዙ ሕዝብ መካከል ይፈርዳል፤
በሩቅና በቅርብ ባሉ ኀያላን መንግሥታት መካከል ያለውን ግጭት ያቆማል፤
ሰይፋቸውን ማረሻ፣
ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጉታል።
አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤
ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም።
4እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣
ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤
የሚያስፈራቸው አይኖርም፤
የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍ ተናግሯልና።
5አሕዛብ ሁሉ፣
በአማልክታቸው ስም ይሄዳሉ፤
እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም፣
ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።
የእግዚአብሔር ዕቅድ
6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“በዚያች ቀን ሽባውን እሰበስባለሁ፤
ስደተኞችንና ለሐዘን ያደረግኋቸውን፣
ወደ አንድ ቦታ አመጣለሁ።
7የሽባዎችን ትሩፍ፣
የተገፉትንም ብርቱ ሕዝብ አደርጋለሁ፤
ከዚያች ቀን አንሥቶ እስከ ዘላለም፣
እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።
8አንተ የመንጋው መጠበቂያ ማማ ሆይ፤
የጽዮን ሴት ልጅ ዐምባ#4፥8 ወይም ኰረብታ ሆይ፤
የቀድሞው ግዛትህ ይመለስልሃል፤
የመንግሥትም ሥልጣን ለኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ይሆናል።”
9አሁንስ እንደዚህ የምትጮኺው ለምንድን ነው?
ንጉሥ የለሽምን?
ምጥ እንደ ያዛት ሴት የተጨነቅሽው፣
መካሪሽ#4፥9 ወይም መሪ ስለ ጠፋ ነውን?
10የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፤
ምጥ እንደ ያዛት ሴት ተጨነቂ፤
አሁንስ ከከተማ ወጥተሽ፣
በሜዳ ላይ መስፈር አለብሽና፤
ወደ ባቢሎን ትሄጃለሽ፤
በዚያ ከጠላት እጅ ትድኛለሽ።
እግዚአብሔር በዚያ፣
ከጠላቶችሽ ይታደግሻል።
11አሁን ግን ብዙ አሕዛብ፣
በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል፤
እነርሱም፣ “የረከሰች ትሁን፤
ዐይናችንም ጽዮንን መዘባበቻ አድርጎ ይያት” ይላሉ።
12ነገር ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ አያውቁም፤
በዐውድማ ላይ እንደ ነዶ የሚሰበስባቸውን፣
የርሱን ዕቅድ አያስተውሉም።
13“የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ተነሥተሽ አበራዪ፤
የብረት ቀንድ እሰጥሻለሁና፤
የናስ ሰኰና እሰጥሻለሁ፤
አሕዛብንም ታደቅቂአቸዋለሽ።”
በግፍ ያግበሰበሱትን ትርፍ ለእግዚአብሔር፣
ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ ትለዪአለሽ።
Currently Selected:
ሚክያስ 4: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.