ማቴዎስ 27:32-44

ማቴዎስ 27:32-44 NASV

ይዘውትም ሲሄዱ ስምዖን ተብሎ የሚጠራ የቀሬና ሰው አገኙ፤ መስቀሉንም እንዲሸከም አስገደዱት። ትርጕሙ፣ “የራስ ቅል ስፍራ” ከሆነው ጎልጎታ ከተባለው ቦታ ሲደርሱ፣ ከሐሞት ጋራ የተቀላቀለ የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን ቀምሶ ሊጠጣው አልፈቀደም። ከሰቀሉትም በኋላ ዕጣ ጥለው ልብሱን ተካፈሉ፤ በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር። ከራስጌውም፣ “ይህ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ነው” የሚል የክስ ጽሑፍ አኖሩ። ሁለት ወንበዴዎች አንዱ በቀኙ፣ አንዱ በግራው ዐብረውት ተሰቅለው ነበር። በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ፤ እስኪ ራስህን አድን! የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ!” ይሉት ነበር። የካህናት አለቆችም ከኦሪት ሕግ መምህራንና ከሽማግሌዎች ጋራ ሆነው እያሾፉበት እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም! የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ አሁን ከመስቀል ይውረድ፤ እኛም እናምንበታለን። በእግዚአብሔር ታምኗል፤ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ይል ስለ ነበር እስኪ ከወደደው አሁን ያድነው!” ከርሱ ጋራ የተሰቀሉት ወንበዴዎችም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች