ጧት በማለዳ ላይ፣ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ሁሉ ኢየሱስ ስለሚገደልበት ሁኔታ ተመካከሩ፤ ካሰሩትም በኋላ ወስደው ለገዢው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ኢየሱስ እንደ ተፈረደበት ባየ ጊዜ ተጸጸተ፤ የወሰደውን ሠላሳ ጥሬ ብር ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ ሽማግሌዎች መልሶ በመስጠት፣ “ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ እኛ ምን አገባን፤ የራስህ ጕዳይ ነው!” አሉት። ስለዚህ ይሁዳ ብሩን በቤተ መቅደስ ውስጥ ወርውሮ ወጣ፤ ሄዶም ራሱን ሰቅሎ ሞተ። የካህናት አለቆች ብሩን አንሥተው፣ “የደም ዋጋ ስለ ሆነ ወደ መባ ልንጨምረው አይፈቀድም” አሉ፤ ተመካክረውም ለእንግዶች የመቃብር ስፍራ እንዲሆን በገንዘቡ የሸክላ ሠሪውን ቦታ ገዙበት። ስለዚህም ያ ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት” ተብሎ ይጠራል። በዚህም በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “ለርሱ ዋጋ ይሆን ዘንድ የእስራኤል ልጆች የገመቱትን ሠላሳ ጥሬ ብር ተቀበሉ፤ ጌታም ባዘዘኝ መሠረት ለሸክላ ሠሪው ቦታ ከፈሉ።” በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አገረ ገዥው ፊት ቀረበ፤ አገረ ገዥውም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” በማለት ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አንተው እንዳልኸው ነው” ሲል መለሰለት። የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲከስሱት ግን ምንም መልስ አልሰጠም። በዚህ ጊዜ ጲላጦስ፣ “ስንት ነገር አቅርበው እንደሚከስሱህ አትሰማምን?” አለው። እርሱ ግን አገረ ገዥው እስኪገረም ድረስ ለቀረበበት ክስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰም።
ማቴዎስ 27 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 27
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 27:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች