የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 26:36-75

ማቴዎስ 26:36-75 NASV

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እነርሱንም፣ “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ከእርሱም ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ሄዶ ይተክዝና ይጨነቅ ጀመር፤ ከዚያም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ ዐዝናለች፤ ከእኔ ጋር በመትጋት እዚሁ ቈዩ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎ በግንባሩ በመደፋት፣ “አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” ብሎ ጸለየ። ከዚያም ተመልሶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ፣ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ፤ ከእኔ ጋር ለአንድ ሰዓት እንኳ መትጋት አቃታችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ፣ “አባት ሆይ፤ ይህ ሳልጠጣው የማያልፍ ጽዋ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይፈጸም” ብሎ ጸለየ። እንደ ገናም በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር ተኝተው አገኛቸው። ትቷቸውም እንደ ገና በመሄድ ለሦስተኛ ጊዜ ቀደም ብሎ የጸለየውን ጸሎት ደገመ። ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ዐርፋችሁ ተኝታችኋል? እነሆ፣ ሰዓቱ ቀርቧል፤ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ ተነሡ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝም እየመጣ ነው።” በመናገር ላይ እያለ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ የተላኩ ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ። ይሁዳም፣ “እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቷቸው ስለ ነበር፣ በቀጥታ ወደ ኢየሱስ ሄዶ፣ “መምህር ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት ሳመው። ኢየሱስም፣ “ወዳጄ ሆይ፤ የመጣህበትን ፈጽም” አለው። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ቀርበው ኢየሱስን ያዙት፤ አሰሩትም። ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ። ካስፈለገ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ክፍለ ሰራዊት የሚበልጡ መላእክት የማይሰድድልኝ ይመስልሃል? ይህ ቢሆን ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት ይሆናል ያሉት ነገር እንዴት ይፈጸማል?” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁ? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ ሳስተምር አልያዛችሁኝም ነበር፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው ነቢያት በቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩት ይፈጸም ዘንድ ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ጥለውት ሸሹ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፣ የኦሪት የሕግ መምህራንና የሕዝብ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ነበሩበት፣ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ነገር ግን ጴጥሮስ ከርቀት ሆኖ እስከ ሊቀ ካህናቱ ቅጥር ግቢ ይከተለው ነበር፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የሁኔታውን መጨረሻ ለማየት ከጠባቂዎች ጋር ተቀመጠ። በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ በሙሉ ኢየሱስን ለማስገደል የሐሰት ማስረጃ ይፈልጉ ነበር፤ ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም በቂ ማስረጃ አላገኙም፤ በኋላ ግን ሁለት ሰዎች ቀርበው፣ “ይህ ሰው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ውስጥ መልሼ ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል” በማለት ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ተነሥቶ በመቆም፣ “እነዚህ ሰዎች ለሚመሰክሩብህ ሁሉ ምንም መልስ አትሰጥምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም፣ “በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ ንገረን” አለው። ኢየሱስም፣ “አንተው ራስህ ብለኸዋል፤ ነገር ግን ለሁላችሁም ልንገራችሁ፤ ወደ ፊት የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው። በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀድዶ፣ “በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሯል፤ ከዚህ ሌላ ምን ምስክርነት ያስፈልገናል? በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል መናገሩን እናንተው ራሳችሁ ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ። በዚህ ጊዜ ፊቱ ላይ እየተፉ በጡጫ መቱት፤ ሌሎቹም በጥፊ እየመቱት፣ “ክርስቶስ ሆይ፤ ማነው የመታህ? እስቲ ትንቢት ንገረን!” አሉት። ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ተቀምጦ ሳለ አንዲት የቤት ሠራተኛ ወደ እርሱ ቀርባ፣ “አንተም ከገሊላው ኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው። እርሱ ግን፣ “ምን እንደምትናገሪ አላውቅም” በማለት በሁላቸውም ፊት ካደ። ከግቢው መውጫ ወደ ሆነው በር ሲያመራ ሌላዋ ሠራተኛ ተመልክታው፣ በዚያ ለነበሩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር” አለች። እርሱም በመሐላ ቃል፣ “ሰውየውን አላውቀውም!” ሲል ዳግመኛ ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በዚያ ቆመው የነበሩት ሰዎች ቀርበው ጴጥሮስን፣ “አነጋገርህ ስለሚያጋልጥህ፣ በርግጥ አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ!” አሉት። እርሱም እየማለና እየተገዘተ፣ “እኔ ሰውየውን አላውቀውም!” አላቸው። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ፣ “ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለው፤ ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች