የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማቴዎስ 25:1-30

ማቴዎስ 25:1-30 NASV

“በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ልጃገረዶችን ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ልጃገረዶች ዝንጉዎች፣ አምስቱ ደግሞ አስተዋዮች ነበሩ፤ ዝንጉዎቹ መብራት ይዘው መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር። አስተዋዮቹ ግን ከመብራታቸው ጋር መጠባበቂያ ዘይት በማሰሮ ይዘው ነበር። ሙሽራው በዘገየ ጊዜ፣ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ። “እኩለ ሌሊት ላይ፣ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጥሪ ተሰማ። “በዚህ ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሥተው መብራቶቻቸውን እየተረኰሱ መዘጋጀት ያዙ። ዝንጉዎቹ አስተዋዮቹን፣ ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለሆነ፣ ከዘይታችሁ ስጡን’ አሏቸው። “አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ግን መልሰው፣ ‘ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፣ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ’ አሏቸው። “ዘይት ሊገዙ እንደ ሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ልጃገረዶችም ወደ ሰርጉ ግብዣ አብረውት ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። “ዘግየት ብለው ሌሎቹ ልጃገረዶች መጥተው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በሩን ክፈትልን’ አሉ። “እርሱ ግን መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው። “እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ። “የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጕዞውን ቀጠለ። አምስት ታላንት የተቀበለው ሰውየ፣ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት ታላንት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ። “የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ። አምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ! አምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ አምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው። “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው። “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ ታላንትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው። “ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ አገልጋይ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሯል? ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር። “ ‘በሉ እንግዲህ ታላንቱን ወስዳችሁ ዐሥር ታላንት ላለው ስጡ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ የተትረፈረፈም ይኖረዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ይህን የማይረባ አገልጋይ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች

Free Reading Plans and Devotionals related to ማቴዎስ 25:1-30