ኢየሩሳሌም መቃረቢያ ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደምትገኘው ቤተ ፋጌ ወደተባለችው ስፍራ እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤ እንዲህ አላቸው “በፊታችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፤ እንደ ደረሳችሁም አንዲት አህያ ከነውርንጫዋ ታስራ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም ወደ እኔ አምጧቸው። ማንም ሰው ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ ቢላችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልጋሉ፤ እርሱም ወዲያውኑ መልሶ ይልካቸዋል’ በሉት።” ይህ የሆነውም በነቢዩ እንዲህ በማለት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው። “ለጽዮን ልጅ እንዲህ በሏት፤ ‘እነሆ፤ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ፣ በአህያዪቱና በግልገሏ፣ በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።’ ” ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። አህያዪቱንና ውርንጫዋን አምጥተው ልብሶቻቸውን በላያቸው ላይ አኖሩ፤ እርሱም ተቀመጠባቸው። ከሕዝቡም አብዛኛው ልብሶቻቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎቹም ከዛፎች ቅርንጫፍ እየዘነጠፉ በመንገዱ ላይ ያነጥፉ ነበር። ቀድሞት የሚሄደውና ይከተለው የነበረው ሕዝብም እንዲህ እያለ ይጮኽ ነበር፤ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ!” “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!” “ሆሳዕና በአርያም!” ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜም ከተማዋ በመላ፣ “ይህ ማነው?” በማለት ታወከች። ሕዝቡም፣ “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚሸጡትንና የሚገዙትን አስወጣቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ በመገለባበጥ፣ “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን፣ ‘የወንበዴዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው። በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዐይነ ስውሮችና ሽባዎች ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና የኦሪት ሕግ መምህራን ያደረጋቸውን ታምራትና፣ “ሆሳዕና፤ ለዳዊት ልጅ” እያሉ በመቅደስ የሚጮኹትን ሕፃናት ባዩ ጊዜ በቍጣ ተሞሉ። እነርሱም፣ “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህ?” አሉት። ኢየሱስም፣ “አዎን እሰማለሁ፤ እንዲህ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን? “ ‘ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ፣ ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ።’ ” ትቷቸው ከከተማው ወጣ፤ ወደ ቢታንያም ሄዶ በዚያው ዐደረ።
ማቴዎስ 21 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 21
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 21:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos