ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት በአንድነት ጠርቶ አጋንንትን ሁሉ እንዲያወጡ፣ ደዌንም እንዲፈውሱ ኀይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩና የታመሙትን እንዲፈውሱ ላካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ለመንገዳችሁ በትር ቢሆን፣ ከረጢትም ቢሆን፣ እንጀራም ቢሆን፣ ገንዘብም ቢሆን፣ ሁለት ሁለት እጀ ጠባብም መያዝ አያስፈልጋችሁም። ከዚያ ከተማ እስከምትወጡ ድረስ መጀመሪያ በገባችሁበት በማንኛውም ቤት ቈዩ። የከተማው ሰዎች ሳይቀበሏችሁ ቀርተው ከተማቸውን ለቅቃችሁ ስትሄዱ፣ ምስክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ።” እነርሱም በዚሁ መሠረት ወጥተው ወንጌልን እየሰበኩ በየቦታው ሁሉ ሕመምተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም፣ በዚህ ጊዜ የሆነውን ነገር ሁሉ ሰምቶ በሁኔታው ተደናገረ፤ ምክንያቱም አንዳንድ ሰዎች ዮሐንስ ከሙታን እንደ ተነሣ ያወሩ ነበር፤ ሌሎች ኤልያስ እንደ ተገለጠ፣ ሌሎች ደግሞ ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሙታን እንደ ተነሣ ይናገሩ ነበር። ሄሮድስም፣ “መጥምቁ ዮሐንስን እኔው ራሴ ዐንገቱን አስቈርጬው ሞቷል፤ ታዲያ፣ ስለ እርሱ እንዲህ ሲወራ የምሰማው ይህ ሰው ማነው?” አለ፤ በዐይኑም ሊያየው ይሻ ነበር። ሐዋርያትም ተመልሰው በመጡ ጊዜ ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት፤ እርሱም ይዟቸው ቤተ ሳይዳ ወደምትባል ከተማ በመሄድ ለብቻው ገለል አለ። ሕዝቡም ይህንኑ ዐውቀው ተከተሉት፤ እርሱም ተቀብሏቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስ የሚያስፈልጋቸውንም ፈወሳቸው። ቀኑም ሊመሽ ሲል፣ ዐሥራ ሁለቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ያለነው በምድረ በዳ ስለሆነ፣ ሕዝቡ ወደ አካባቢው መንደርና ገጠር ሄደው ማደሪያና ምግብ እንዲፈልጉ አሰናብታቸው” አሉት። እርሱ ግን፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ሄደን ካልገዛን በስተቀር፣ እኛ ያለን ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ አይበልጥም” አሉት፤ አምስት ሺሕ ያህል ወንዶች በዚያ ነበሩና። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሕዝቡን በአምሳ በአምሳ ሰው መድባችሁ አስቀምጧቸው” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም በታዘዙት መሠረት ሰዎቹ እንዲቀመጡ አደረጉ። እርሱም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ እያየ ባረካቸው፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ከእነርሱ የተረፈውን ቍርስራሽ እንጀራ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ይጸልይ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ እርሱም፣ “ሕዝቡ እኔን ማን ነው ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ከቀድሞ ነቢያት አንዱ ከሙታን ተነሥቷል ይላሉ” አሉት። እርሱም፣ “እናንተስ ማን ነው ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም፣ “አንተ የእግዚአብሔር መሲሕ ነህ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሓፍት ዘንድ መናቅ፣ መገደልና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን መነሣት አለበት” አላቸው። ከዚያም ለሁሉም እንዲህ አላቸው፤ “በኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየዕለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ምክንያቱም ነፍሱን ሊያድናት የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ ብሎ የሚያጠፋት ግን ያድናታል። ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ጥቅሙ ምንድን ነው? ማንም በእኔና በቃሌ ቢያፍር፣ የሰው ልጅ በራሱ ክብር እንዲሁም በአብና በቅዱሳን መላእክት ክብር ሲመጣ ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔርን መንግሥት ሳያዩ ሞትን የማይቀምሱ ሰዎች አሉ።” ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ሊጸልይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ። በመጸለይ ላይ እንዳለም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ የሚያንጸባርቅ ነጭ ሆነ። እነሆ፤ ሁለት ሰዎች፣ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ በክብርም ተገልጠው፣ በኢየሩሳሌም ይፈጸም ዘንድ ስላለው ከዚህ ዓለም ስለ መለየቱ ይናገሩ ነበር። ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት ግን እንቅልፍ ተጭኗቸው ነበር፤ ሲነቁ ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር የቆሙትን ሁለት ሰዎች አዩ። ሰዎቹም ከኢየሱስ ተለይተው ሲሄዱ፣ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ እዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ሦስት ዳስ እንሥራ፤ አንዱ ለአንተ፣ አንዱ ለሙሴ፣ አንዱም ለኤልያስ ይሆናል” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር። ይህንም እየተናገረ ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ፈሩ። ከደመናውም ውስጥ፣ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም በተሰማ ጊዜ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ፤ ደቀ መዛሙርቱም ነገሩን በልባቸው ያዙ እንጂ ስላዩት ነገር በዚያን ወቅት ለማንም አልተናገሩም። በማግስቱም ከተራራው ከወረዱ በኋላ፣ ብዙ ሕዝብ መጥቶ ኢየሱስን አገኘው። በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “መምህር ሆይ፤ ያለኝ ልጅ እርሱ ብቻ ስለሆነ፣ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ። መንፈስ ሲይዘው በድንገት ይጮኻል፤ ዐረፋ እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፤ ጕዳትም ካደረሰበት በኋላ በስንት መከራ ይተወዋል፤ ደቀ መዛሙርትህ እንዲያወጡለት ለመንኋቸው፤ ነገር ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም “እምነት የለሽ ጠማማ ትውልድ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? በል ልጅህን ወደዚህ አምጣው” አለ። ልጁ በመምጣት ላይ ሳለም ጋኔኑ መሬት ላይ ጥሎ አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሥጾ ልጁን ፈወሰው፤ ለአባቱም መልሶ ሰጠው። ሰዎቹም ሁሉ በእግዚአብሔር ታላቅነት ተገረሙ። እርሱ ባደረገው ሁሉ ሰዎች ሁሉ እየተገረሙ ሳሉ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ይህን የምነግራችሁን ነገር ከቶ እንዳትዘነጉ፤ የሰው ልጅ ዐልፎ በሰዎች እጅ ይሰጣልና” አለ። እነርሱ ግን ይህን አባባል አልተረዱም፤ እንዳያስተውሉ ነገሩ ተሰውሮባቸው ነበር፤ መልሰው እንዳይጠይቁትም ፈሩ። ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ክርክር ተነሣ። ኢየሱስም የልባቸውን ሐሳብ ተረድቶ፣ አንድ ሕፃን ይዞ በአጠገቡ አቆመ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ማንም ቢኖር እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ደግሞ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና።” ዮሐንስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየን፤ ከእኛ ጋር ሆኖ ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን” አለው። ኢየሱስም፣ “አትከልክሉት፤ የማይቃወማችሁ ሁሉ እርሱ ከእናንተ ጋር ነውና” አለው።
ሉቃስ 9 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 9
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 9:1-50
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos