በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ግን፣ “በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሏቸው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት በተራበ ጊዜ ከባልንጀሮቹ ጋራ ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኅብስተ ገጽ ወስዶ በላ፤ ዐብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።” ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው። በሌላ ሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ። ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ሊከስሱት ምክንያት በመፈለግ፣ በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እጁ የሰለለችበትን ሰው፣ “ተነሥተህ መካከል ላይ ቁም” አለው፤ ሰውየውም ተነሥቶ ቆመ። ኢየሱስም፣ “እስኪ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነው ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። ደግሞም ኢየሱስ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደ ተባለው አደረገ፤ እጁም ፈጽሞ ዳነለት። ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ግን በቍጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም እርስ በርስ ተወያዩ። ከእነዚያም ቀናት በአንዱ ኢየሱስም ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጥቶ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ ዐደረ። ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ ከእነርሱ ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ እነዚህንም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ እነርሱም፣ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀነናዊው የተባለው ስምዖን፣ የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበሩ። ኢየሱስም ዐብሯቸው ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም እጅግ ብዙ ሰዎች በዚያ ነበሩ፤ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ጠረፍ የመጣ ብዙ ሕዝብም በዚያ ነበረ፤ እነዚህም የመጡት ሊሰሙትና ካለባቸው ደዌ ሊፈወሱ ነበር። በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩትም ተፈወሱ፤ ኀይል ከርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር።
ሉቃስ 6 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 6
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 6:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች