የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 4:1-13

ሉቃስ 4:1-13 NASV

ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ እንደ ተመለሰ፣ መንፈስ ወደ በረሓ ወሰደው፤ በዚያም አርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ፤ በእነዚያም ቀናት ምንም ሳይበላ ቈይቶ በመጨረሻ ተራበ። ዲያብሎስም፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ እስቲ ይህ ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዘው” አለው። ኢየሱስም፣ “ ‘ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ብሎ መለሰለት። ከዚያም ዲያብሎስ ወደ አንድ ከፍታ ቦታ አውጥቶት የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው፤ እንዲህም አለው፤ “የእነዚህ መንግሥታት ሥልጣንና ክብር ሁሉ ለእኔ ተሰጥቷል፤ እኔም ለምወድደው ስለምሰጥ፣ ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል።” ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፏል” አለው። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ወስዶ በቤተ መቅደስ ጕልላት ላይ አቆመውና እንዲህ አለው፤ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ እስቲ ራስህን ከዚህ ወደ ታች ወርውር፤ ምክንያቱም እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ “ ‘ይጠብቁህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋል፤ እግርህም ከድንጋይ ጋር እንዳይጋጭ፣ በእጆቻቸው ወደ ላይ አንሥተው ይይዙሃል።’ ” ኢየሱስም፣ “ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሏል” ብሎ መለሰለት። ዲያብሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ ከእርሱ ተለየ።