ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ ያመጡ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ባዩ ጊዜ ገሠጿቸው። ኢየሱስ ግን ሕፃናቱን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።” ከአይሁድ አለቆች አንዱ፣ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም፤ ‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ትእዛዝ ታውቃለህ።” ሰውየውም፣ “እነዚህንማ ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ” አለው። ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ “እንግዲያውስ አንድ ነገር ይቀርሃል፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ ሀብት ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው። ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ፣ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው በጣም ዐዘነ። ኢየሱስም ሰውየውን ተመልክቶ እንዲህ አለ፤ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ምንኛ ከባድ ነው! ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።” ይህን የሰሙ ሰዎችም፣ “ታዲያ፣ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ። ኢየሱስም፣ “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” አለ። ጴጥሮስም፣ “እነሆ፤ እኛ ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሃል” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ለእግዚአብሔር መንግሥት ብሎ ቤቱን ወይም ሚስቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም ወላጆቹን ወይም ልጆቹን የተወ፣ በዚህ ዘመን ብዙ ዕጥፍ፣ በሚመጣውም ዘመን የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”
ሉቃስ 18 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 18
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 18:15-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች