የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 1:1-80

ሉቃስ 1:1-80 NASV

በእኛ መካከል ስለ ተፈጸሙት ነገሮች ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸውን ያህል ጽፈውት ይገኛል፤ ይህም ታሪክ ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩት ያስተላለፉልን ነው። ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ፤ እኔም በበኩሌ ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ፣ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ፤ ይህንም የማደርገው የተማርኸው ነገር እውነተኛ መሆኑን እንድታውቅ ነው። በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን፣ ከአብያ የክህነት ምድብ የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱ ኤልሳቤጥም ከአሮን ነገድ ነበረች። ሁለቱም የጌታን ትእዛዝና ሥርዐት ሁሉ ጠብቀው ያለ ነቀፋ የሚኖሩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ መካን በመሆኗ ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜ የገፉ ነበሩ። አንድ ቀን ዘካርያስ በምድቡ ተራ፣ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ፣ በሥርዐተ ክህነቱ መሠረት፣ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን በዕጣ ተመረጠ። ዕጣን በሚታጠንበትም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆኖ ይጸልይ ነበር። የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቷል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። በእርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ፤ ብዙዎችም እርሱ በመወለዱ ደስ ይላቸዋል፤ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና። የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ በእናቱም ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል። ከእስራኤልም ሰዎች ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፣ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ፣ ለጌታ የተገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት በኤልያስ መንፈስና ኀይል በጌታ ፊት ይሄዳል።” ዘካርያስም መልአኩን፣ “ይህን በምን ዐውቃለሁ? እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜ ገፍታለች” አለው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን እነግርህና ይህን የምሥራች አመጣልህ ዘንድ ተልኬአለሁ፤ እነሆ፤ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፣ ይህም እስከሚፈጸምበት ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።” በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ዘካርያስ ከቤተ መቅደሱ ሳይወጣ ለምን እንደ ዘገየ በመገረም ይጠባበቅ ነበር። ከወጣ በኋላም ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በምልክት ከመጥቀስ በስተቀር መናገር ባለ መቻሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ። ዘካርያስም የአገልግሎቱ ወቅት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ከዚህ በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ አምስት ወራትም ራሷን ሰወረች፤ እርሷም፣ “ጌታ በምሕረቱ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ሊያስወግድልኝ ተመልክቶ በዚህ ጊዜ ይህን አድርጎልኛል” አለች። በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ከተማ ላከው፤ የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት። ማርያምም በንግግሩ እጅግ በጣም ደንግጣ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” እያለች ነገሩን ታሰላስል ጀመር፤ መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።” ማርያምም መልአኩን፣ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው። መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። እነሆ፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተ እርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን የተባለችውም ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።” ማርያምም፣ “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቷት ሄደ። ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤ ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሏልና። ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!” ማርያምም እንዲህ አለች፤ “ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤ እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷልና። ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤ ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቷል፤ በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኗቸዋል፤ ገዦችን ከዙፋናቸው አውርዷቸዋል፤ ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል፤ የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቧቸዋል፤ ሀብታሞችን ግን ባዷቸውን ሰድዷቸዋል፤ ምሕረቱን በማስታወስ፣ ባሪያውን እስራኤልን ረድቷል፤ ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣ ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።” ማርያምም ሦስት ወር ያህል ኤልሳቤጥ ዘንድ ከቈየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች። የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ቀን ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶቿና ዘመዶቿም ጌታ ታላቅ ምሕረት እንዳደረገላት ሰሙ፤ የደስታዋም ተካፋዮች ሆኑ። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ፈለጉ፤ እናቱ ግን፣ “አይሆንም፤ ዮሐንስ መባል አለበት” አለች። እነርሱም፣ “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” አሏት። አባቱንም ምን ስም ሊያወጣለት እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት። እርሱም መጻፊያ ሰሌዳ እንዲሰጡት ለምኖ፣ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በነገሩ ተደነቁ። ወዲያውም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱ ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ መናገር ጀመረ። ጎረቤቶቹም ሁሉ በፍርሀት ተሞሉ፤ ይህም ሁሉ ነገር በደጋማው የይሁዳ ምድር ሁሉ ተወራ። ይህንም የሰሙ ሁሉ፣ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ነገሩን በልባቸው ያዙ፤ የጌታ እጅ በርግጥ ከእርሱ ጋር ነበርና። የሕፃኑም አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፤ “የእስራኤል አምላክ፣ ጌታ ይመስገን፤ መጥቶ ሕዝቡን ተቤዥቷልና። በባሪያው በዳዊት ቤት፣ የድነት ቀንድ አስነሥቶልናል፤ ይህም ጥንት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው፣ ማዳኑም ከጠላቶቻችንና፣ ከተፃራሪዎቻችን ሁሉ እጅ ነው፤ ይህንም ያደረገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየት፣ ቅዱስ ኪዳኑን ለማስታወስ፣ ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ለማሰብ፣ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶ፣ ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው፣ በዘመናችንም ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ ሊያቆመን ነው። “ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፤ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ የጌታን መንገድ ለማዘጋጀት በፊቱ ትሄዳለህና፤ የኀጢአታቸውን ስርየት ከማግኘታቸው የተነሣ፤ ለሕዝቡ የመዳንን ዕውቀት ትሰጥ ዘንድ፣ ከአምላካችንም በጎ ምሕረት የተነሣ፣ የንጋት ፀሓይ ከሰማይ ወጣችልን፤ ይኸውም በጨለማ ለሚኖሩት፣ በሞት ጥላ ውስጥም ላሉት እንዲያበራና፣ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ እንዲመራ ነው።” ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤልም ሕዝብ በይፋ እስከ ታየበት ቀን ድረስ በበረሓ ኖረ።