የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘሌዋውያን 25

25
የሰባተኛው ዓመት ዕረፍት
1 እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፤ 2“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ወደምሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ ምድሪቱ ራሷ የእግዚአብሔርን ሰንበት ታክብር። 3ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ ስድስት ዓመት ወይንህን ግረዝ፤ ፍሬውንም ሰብስብ። 4በሰባተኛው ዓመት ግን ምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ታድርግ፤ ይህም የእግዚአብሔር ሰንበት ነው። በዕርሻህ ላይ አትዝራ፤ ወይንህንም አትግረዝ። 5ሳይዘራ የበቀለውን አትጨደው፤ ካልተገረዘው የወይን ተክልህ ፍሬ አትሰብስብ። ምድሪቱ የአንድ ዓመት ዕረፍት ታድርግ። 6ምድሪቱም በሰንበት ጊዜዋ የምታስገኘው ማንኛውም ፍሬ ለአንተ፣ ለወንድ ባሪያህ፣ ለሴት ባሪያህ፣ ለቅጥር ሠራተኛህና ከአንተ ጋራ ለሚኖር መጻተኛ ምግብ ይሁን፤ 7እንዲሁም ለቤት እንስሳትህና በምድርህ ለሚኖሩ የዱር አራዊት ምድሪቱ የምታበቅለው ሁሉ መኖ ይሁን።
የኢዮቤልዩ ዓመት
25፥8-38 ተጓ ምብ – ዘዳ 15፥1-11
25፥39-55 ተጓ ምብ – ዘፀ 21፥2-11ዘዳ 15፥12-18
8“ ‘ሰባት የሰንበት ዓመታት ማለትም ሰባት ጊዜ ሰባት ዓመታትን ቍጠር፤ ሰባቱ የሰንበት ዓመታትም አርባ ዘጠኝ ዓመታት ይሆናሉ። 9ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በዐሥረኛው ቀን፣ መለከት ይነፋ፤ በማስተስረያ ቀንም በምድራችሁ ሁሉ መለከት ንፉ። 10ዐምሳኛውን ዓመት ቀድሱ፤ በምድሪቱ ሁሉ ላሉ ነዋሪዎች በሙሉ ነጻነት ዐውጁ፤ ይህም ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደ ቤተ ሰቡ ርስት፣ ወደ ወገኑም ይመለስ። 11የኀምሳኛው ዓመት ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ አትዝሩ፤ ሳትዘሩት የበቀለውን አትጨዱ፤ ካልተገረዘውም የወይን ሐረግ ፍሬ አትሰብስቡ። 12ኢዮቤልዩ ስለ ሆነ ለእናንተ የተቀደሰ ይሁን፤ ሳትዘሩት በሜዳ የበቀለውን ብሉ።
13“ ‘በዚህ በኢዮቤልዩ ዓመት እያንዳንዱ ሰው ወደ ርስቱ ይመለስ።
14“ ‘ከወገንህ ከአንዱ መሬት ብትገዛ ወይም ብትሸጥለት፣ አንዱ ሌላውን አያታልል። 15ከኢዮቤልዩ በኋላ ያሉትን ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ከወገንህ ትገዛለህ፤ እርሱም የቀሩትን የመከር ዓመታት ብዛት መሠረት በማድረግ ይሸጥልሃል። 16የዓመቱ ቍጥር ከበዛ ዋጋውን ጨምር፤ የዓመቱ ቍጥር ካነሰም፣ ዋጋውን ቀንስ፤ ምክንያቱም የሚሸጥልህ የዓመቱን የምርት መጠን ነውና። 17አንዱ ሌላውን አያታልል፤ አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
18“ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤ ሕጌን በጥንቃቄ አድርጉ፤ በምድሪቱም ያለ ሥጋት ትኖራላችሁ። 19ምድሪቱ ፍሬዋን ትሰጣለች፤ እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በዚያም ያለ ሥጋት ትኖራላችሁ። 20እናንተም፣ “ካልዘራን ወይም ሰብላችንን ካልሰበሰብን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?” በማለት ትጠይቁ ይሆናል። 21በስድስተኛው ዓመት በረከቴን እሰድድላችኋለሁ፤ ምድሪቱም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ፍሬ ትሰጣለች። 22በስምንተኛው ዓመት በምትዘሩበት ጊዜ፣ የምትበሉት ቀድሞ ከሰበሰባችሁት ሰብል ይሆናል፤ የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስክትሰበስቡ ድረስ ከዚሁ እህል ትበላላችሁ።
23“ ‘መሬት ለዘለቄታ አይሸጥ፤ ምክንያቱም ምድሪቱ የእኔ ናት፤ እናንተም መጻተኞችና እንግዶች ናችሁ። 24ርስት አድርጋችሁ በምትይዙት ምድር ሁሉ መሬት የሚዋጅበት ሁኔታ እንዲኖር አድርጉ።
25“ ‘ከወገንህ አንዱ ደኽይቶ ርስቱን ቢሸጥ፣ የቅርብ ዘመዱ መጥቶ ወገኑ የሸጠውን ይዋጅለት። 26ነገር ግን ሰውየው ርስቱን የሚዋጅለት ምንም ዘመድ ባይኖረውና እርሱ ራሱ መዋጀት የሚችልበትን ሀብት ቢያገኝ፣ 27ርስቱን ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የሽያጭ ዘመን በመቍጠር የዋጋውን ልዩነት ለገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ገዛ ርስቱ ይመለስ። 28ነገር ግን ዋጋውን መመለስ ካልቻለ፣ የሸጠው ርስት እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የገዢው ንብረት ሆኖ ይቈያል፤ በኢዮቤልዩ ዓመት ለባለቤቱ ይመለሳል፤ ሰውየውም ወደ ርስቱ ይመለሳል።
29“ ‘ማንኛውም ሰው ቅጥር በተሠራለት ከተማ ውስጥ የሚገኝ መኖሪያ ቤቱን ቢሸጥ ከሸጠበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት ሊዋጀው ይችላል፤ የመዋጀት መብቱ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ነው። 30ሙሉው ዓመት ከማለቁ በፊት መዋጀት ካልቻለ ግን፣ ቅጥር በተሠራለት ከተማ ውስጥ ያለው ቤት የገዢውና የልጅ ልጆቹ ንብረት ሆኖ ይቀራል፤ በኢዮቤልዩ አይመለስለትም። 31ቅጥር በዙሪያው ባልተሠራለት መንደር ውስጥ የሚገኙ ቤቶች ግን እንደ ዕርሻ መሬት ተቈጥረው ሊዋጁ ይችላሉ፤ በኢዮቤልዩም ይመለሳሉ።
32“ ‘ነገር ግን ሌዋውያን የራሳቸው በሆኑት ከተሞች ውስጥ የሚገኙትን ቤቶቻቸውን ምን ጊዜም የመዋጀት መብት አላቸው። 33ሌዋውያን በከተማቸው ያለውን ቤታቸውን ቢሸጡና መዋጀት ባይችሉ፣ በኢዮቤልዩ ይመለሳል፤ በሌዋውያን ከተሞች የሚገኙ ቤቶች በእስራኤላውያን መካከል የሌዋውያን ንብረት ናቸውና። 34በከተሞቻቸው ዙሪያ ያለው የግጦሽ መሬት ግን አይሸጥ፤ ለዘላለም ቋሚ ንብረታቸው ነውና።
35“ ‘በመካከልህ ከወገንህ አንዱ ቢደኸይ፣ ራሱንም መርዳት ባይችል፣ በመካከልህ ይኖር ዘንድ መጻተኛውን ወይም እንግዳውን እንደምትረዳ ርዳው። 36ወገንህ በመካከልህ ይኖር ዘንድ ምንም ዐይነት ወለድ#25፥36 ወይም እጅግ ብዙ ወለድ፤ እንዲሁም 37 ይመ አትቀበለው፤ አምላክህን ፍራው። 37ገንዘብህን በዐራጣ አታበድረው፤ ምግብህንም በትርፍ አትሽጥለት። 38የከነዓንን ምድር ልሰጥህና አምላክህ ልሆን፣ ከግብጽ ያወጣሁህ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ።
39“ ‘ከወገንህ አንዱ ከመካከልህ ቢደኸይ፣ ራሱንም ለአንተም ቢሸጥ፣ እንደ ባሪያ አድርገህ አታሠራው። 40በመካከልህ እንዳለ ቅጥር ሠራተኛ ወይም እንደ እንግዳ አድርገህ ቍጠረው፤ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመትም ይሥራልህ፤ 41ከዚያም በኋላ እርሱና ልጆቹ በነጻ ይለቀቁ፤ ወደ ቤተ ሰቡና ወደ አባቶቹ ንብረት ይመለስ። 42እስራኤላውያን ከግብጽ ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ስለ ሆኑ እንደ ባሪያ አይሸጡ። 43በጭካኔ አትግዛቸው፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።
44“ ‘የሚኖሩህ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችህ፣ በዙሪያህ ካሉት አሕዛብ መካከል የገዛሃቸው ባሪያዎች ይሁኑ። 45እንደዚሁም በመካከላችሁ ከሚኖሩት መጻተኞችና ከተወለዱት ወገናቸው ባሪያዎችን ግዙ፤ ንብረታችሁም ይሁኑ። 46እነርሱንም እንደ ንብረት ለልጆቻችሁ አውርሷቸው፤ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ባሪያዎች ይሁኗችሁ፤ እስራኤላውያን ወገኖቻችሁን ግን በጭካኔ አትግዟቸው።
47“ ‘በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆንና ከወገናችሁ አንዱ ደኽይቶ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ ወይም ከመጻተኛው ወገን ለአንዱ ራሱን ቢሸጥ፣ 48ከተሸጠ በኋላ ሊዋጅ ይችላል። ከዘመዶቹም አንዱ፣ 49አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ወይም ከወገኖቹ ማንኛውም የሥጋ ዘመዱ ይዋጀው፤ ሀብት ካገኘም ራሱን መዋጀት ይችላል። 50እርሱም ራሱን ከሸጠበት ዓመት አንሥቶ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ ከገዛው ሰው ጋራ በመሆን ይቍጠር፤ ነጻ የሚለቀቅበትም ዋጋ በእነዚያ ዓመታት ለአንድ ቅጥር ሠራተኛ በሚከፈለው መሠረት ይተመናል። 51ብዙ ዓመት የሚቀረው ከሆነም፣ እርሱን ለመግዛት ከተከፈለው ዋጋ ላይ በቀረው ዓመት መጠን ለሚዋጅበት መልስ ይክፈል። 52እስከ ኢዮቤልዩ ድረስ የሚቀረው ጥቂት ዓመት ከሆነም፣ በቀረው ዓመት መጠን የሚዋጅበትን መልስ ይክፈል። 53ከዓመት እስከ ዓመት እንደ ቅጥር ሠራተኛ ይኑር፤ አሳዳሪውም በፊትህ በጭካኔ አይግዛው።
54“ ‘ከእነዚህ መንገዶች በአንዱ እንኳ መዋጀት ባይችል፣ እርሱና ልጆቹ በኢዮቤልዩ ዓመት በነጻ ይለቀቁ፤ 55እስራኤላውያን ለእኔ አገልጋዮቼ ናቸውና። እነርሱ ከግብጽ ምድር ያወጣኋቸው አገልጋዮቼ ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

Currently Selected:

ዘሌዋውያን 25: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ