ዘሌዋውያን 24
24
በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ ዘይትና ኅብስት
24፥1-3 ተጓ ምብ – ዘፀ 27፥20-21
1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“መብራቶቹ ያለማቋረጥ እንዲያበሩ ለመብራቱ የሚሆን ከወይራ ተጨምቆ የተጠለለ ንጹሕ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን እዘዛቸው። 3አሮንም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከምስክሩ ታቦት መጋረጃ ውጭ በእግዚአብሔር ፊት ያሉትን መብራቶች ከምሽት እስከ ንጋት ያለ ማቋረጥ ያሰናዳቸው፤ ይህም ከትውልድ እስከ ትውልድ ሥርዐት ነው። 4በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ የወርቅ መቅረዝ ላይ ያሉት መብራቶች ያለ ማቋረጥ መሰናዳት አለባቸው።
5“የላመ ዱቄት ወስደህ ዐሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ እያንዳንዱ ኅብስትም በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ#24፥5 4.5 ሊትር ገደማ ይሆናል መስፈሪያ ዱቄት ይጋገር። 6እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ረድፍ በእግዚአብሔር ፊት ባለው የንጹሕ ወርቅ ጠረጴዛ ላይ አኑራቸው። 7ከኅብስቱ ጋራ የመታሰቢያ ድርሻ ሆኖ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት እንዲሆን ንጹሕ ዕጣን በእያንዳንዱ ረድፍ ላይ አኑር። 8ኅብስቱ የእስራኤልን ሕዝብ ይወክል ዘንድ ዘወትር በየሰንበቱ በእግዚአብሔር ፊት ይደርደር፤ ይህም የዘላለም ቃል ኪዳን ነው። 9ኅብስቱ የአሮንና የልጆቹ ድርሻ ነው፤ በተቀደሰ ስፍራም ይበሉታል፤ ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ድርሻቸው ነውና።”
እግዚአብሔርን መስደብ የሚያስከትለው ቅጣት
10እናቱ እስራኤላዊት፣ አባቱ ግብጻዊ የሆነ አንድ ሰው በእስራኤላውያን መካከል ወጣ፤ በሰፈርም ውስጥ ከአንድ እስራኤላዊ ጋራ ተጣሉ። 11የእስራኤላዊቱ ልጅ የእግዚአብሔርን ስም በማቃለል ሰደበ፤ ስለዚህም ወደ ሙሴ አመጡት፤ የሰውየው እናት ስም ሰሎሚት ነበር፤ እርሷም ከዳን ወገን የተወለደው የደብራይ ልጅ ነበረች። 12የእግዚአብሔር ፈቃድም ግልጽ እስኪሆንላቸው ድረስ በግዞት አኖሩት።
13 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ 14“ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ አውጣው፤ ሲሳደብ የሰሙት ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ በድንጋይ ይውገረው። 15እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ማንም ሰው አምላኩን ቢሳደብ ኀጢአት ሠርቷልና ይጠየቅበታል። 16የእግዚአብሔርን ስም የሚሳደብ ማንኛውም ሰው ይገደል፤ ማኅበሩ ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ የእግዚአብሔርን ስም ከሰደበ ይገደል።
17“ ‘ሰውን ደብድቦ የገደለ ይገደል። 18የሌላውን ሰው እንስሳ ደብድቦ የገደለ ማንኛውም ሰው ያንኑ ዐይነት እንስሳ ይተካለት። 19ማንኛውም ሰው በባልንጀራው ላይ ጕዳት ቢያደርስ፣ የዚያው ዐይነት ጕዳት ይፈጸምበት፤ 20ይኸውም ስብራት በስብራት፣ ዐይን በዐይን፣ ጥርስ በጥርስ ማለት ነው። በሌላው ሰው ላይ ያደረሰው ጕዳት በርሱም ላይ ይድረስበት፤ 21እንስሳ የገደለ ማንኛውም ሰው በገደለው ፈንታ ይተካ፤ ሰው የገደለ ግን ይገደል። 22ለመጻተኛው ሆነ ለአገር ተወላጅ አንድ ዐይነት ሕግ ይኑራችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ”
23ሙሴም ይህን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ እነርሱም ተሳዳቢውን ከሰፈር ወደ ውጭ ወስደው በድንጋይ ወገሩት፤ እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።
Currently Selected:
ዘሌዋውያን 24: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.