ዘሌዋውያን 2
2
የእህል ቍርባን
1“ ‘ማንኛውም ሰው የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ዱቄቱ የላመ ይሁን፤ ዘይት ያፍስስበት፤ ዕጣንም ይጨምርበት፤ 2ወደ ካህናቱም ወደ አሮን ልጆች ያምጣው። ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ሙሉ ያንሣለት፤ ዕጣኑንም ሁሉ ይውሰደው፤ ይህንም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው። 3የተረፈውም የእህሉ ቍርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ቍርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው።
4“ ‘በማብሰያ ምድጃ የተጋገረ የእህል ቍርባን በምታቀርብበት ጊዜ፣ ከላመ ዱቄት ተዘጋጅቶ እርሾ ሳይገባበት በዘይት ተለውሶ የተጋገረ ኅብስት ይሁን፤ አለዚያም#2፥4 ወይም እንዲሁም ያለ እርሾ በሥሡ ተጋግሮ ዘይት የተቀባ ቂጣ ይሁን። 5የእህል ቍርባንህ በምጣድ የሚጋገር ከሆነ፣ እርሾ ሳይገባበት በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ቂጣ ይሁን። 6ቈራርሰህ ዘይት አፍስስበት፤ ይህ የእህል ቍርባን ነው። 7የእህል ቍርባንህ በመጥበሻ የሚበስል ከሆነ፣ ከላመ ዱቄትና ከዘይት ይዘጋጅ። 8በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀውን የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር አምጥተህ ለካህኑ አስረክብ፤ ካህኑም ወደ መሠዊያው ይወስደዋል፤ 9ካህኑም ከእህሉ ቍርባን ላይ ለመታሰቢያ የሚሆነውን ክፍል ያነሣና በእሳት የሚቃጠል፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 10የተረፈውም የእህሉ ቍርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ቍርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው።
11“ ‘ለእግዚአብሔር በእሳት በምታቀርቡት ቍርባን ውስጥ እርሾ ወይም ማር ጨምራችሁ ማቃጠል ስለማይገባችሁ፣ በምታቀርቡት በማንኛውም የእህል ቍርባን እርሾ አይኑርበት። 12እነዚህን የበኵራት ቍርባን አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ሽታው ደስ የሚያሰኝ ቍርባን ሆነው በመሠዊያ ላይ ለመቃጠል አይቀርቡም። 13የምታቀርበውን የእህል ቍርባን ሁሉ በጨው ቀምመው፤ የአምላክህ የቃል ኪዳን ጨው ከእህል ቍርባንህ አይታጣ፤ በቍርባንህም ላይ ጨው ጨምርበት።
14“ ‘የእህል በኵራት ቍርባን ለእግዚአብሔር በምታመጣበት ጊዜ፣ የተፈተገና በእሳት የተጠበሰ እሸት አቅርብ። 15ዘይት ጨምርበት፤ ዕጣንም በላዩ አስቀምጥ፤ ይህ የእህል ቍርባን ነው። 16ካህኑም ከተፈተገው እህልና ከዘይቱ ወስዶ፣ ከዕጣኑ ሁሉ ጋራ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መታሰቢያ አድርጎ ያቃጥል።
Currently Selected:
ዘሌዋውያን 2: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.