የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢያሱ 11

11
የሰሜን ነገሥታት ድል መሆን
1የአሦር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደ ማዶን ንጉሥ፣ ወደ ዮባብ ንጉሥ፣ ወደ ሺምሮን ንጉሥ፣ ወደ አዚፍ ንጉሥ ላከ። 2እንዲሁም በተራራማው አገር ከኪኔሬት ደቡብ በዓረባ፣ በምዕራቡ ቈላ አገርና ከዶር ኰረብታ#11፥2 ወይም ከዶር ከፍታማ ስፍራ በስተ ምዕራብ ወዳሉት ነገሥታት ላከ፤ 3ደግሞም በምሥራቅና በምዕራብ ወደሚገኙት ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያንና በኰረብታማው አገር ወደሚኖሩት ወደ ኢያቡሳውያን፣ እንዲሁም ደግሞ በምጽጳ ምድር በአርሞንዔም ተራራ ግርጌ ወዳሉት ወደ ኤዊያውያን ነገሥታት መልእክት ላከ። 4እነዚህም ሰራዊታቸውን ሁሉ እጅግ ብዙ ከሆኑ ፈረሶችና ሠረገሎች ጋር ይዘው ወጡ፤ የሰራዊቱም ብዛት በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነበር። 5እነዚህ ሁሉ ነገሥታት እስራኤልን ለመውጋት ኀይላቸውን አስተባብረው በማሮን ውሃ አጠገብ በአንድነት ሰፈሩ።
6 እግዚአብሔር ኢያሱን፣ “እነዚህን ሁሉ ነገ በዚች ሰዓት እንደ ሙት አድርጌ፣ በእስራኤል እጅ አሳልፌ ስለምሰጣቸው አትፍራቸው። የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ትቈርጣለህ፤ ሠረገሎቻቸውንም ታቃጥላለህ” አለው።
7ስለዚህ ኢያሱና ሰራዊቱ ሁሉ በድንገት ወደ ማሮን ውሃ መጥተው ወጓቸው። 8እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ስለ ሰጣቸው ድል አደረጓቸው። በታላቂቱ ሲዶና መንገድ መጨረሻ እስከ ማስሮን፣ በስተ ምሥራቅም እስከ ምጽጳ ሸለቆ ድረስ አሳደዷቸው፤ ከእነርሱም በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም። 9ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቈረጠ፤ ሠረገሎቻቸውንም አቃጠለ።
10በዚያን ጊዜም ኢያሱ ወደ ኋላ ተመልሶ አጾርን ያዘ፤ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለው፤ አጾርም ቀድሞ በእነዚህ ሁሉ መንግሥታት ላይ የበላይነት ነበራት። 11በውስጧ ያሉትን ሁሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እስትንፋስ ካለው ፍጡር አንድ እንኳ ሳያስቀሩ ሁሉንም ደመሰሱ#11፥11 የዕብራይስጡ ቃል በዚህም ሆነ በቍጥር 12፡20 እና 21 ላይ አንድን ሰው ወይም ነገር ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠት ማለት ነው።፤ ራሷን አሦርንም በእሳት አቃጠሏት።
12ኢያሱ እነዚህን የነገሥታት ከተሞች በሙሉና ነገሥታታቸውን ሁሉ ያዘ፤ በሰይፍም ስለት ፈጃቸው፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ባዘዘውም መሠረት ፈጽሞ ደመሰሳቸው። 13ያም ሆኖ ግን ኢያሱ ካቃጠላት ከአጾር በስተቀር፣ እስራኤላውያን በየተራራው ላይ ያሉትን ከተሞች አላቃጠሉም ነበር። 14እስራኤላውያን ምርኮውን በሙሉ፣ ከእነዚህም ከተሞች የተገኙትን እንስሳት ለራሳቸው ወሰዱ፤ ሕዝቡን ግን በሙሉ በሰይፍ ስለት ፈጁት፤ እስትንፋስ ካለው ፍጡር አንድም ሳያስቀሩ ፈጽመው ደመሰሱት። 15እግዚአብሔር ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ፣ ሙሴም ኢያሱን አዘዘው፤ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ካዘዘው ሁሉ እርሱ ያልፈጸመው አንዳች ነገር አልነበረም።
16ኢያሱ ያንን ምድር በሙሉ፣ ማለት ተራራማውን አገር፣ ኔጌቭን ሁሉ፣ የጎሶምን ምድር በሙሉ፣ የምዕራቡን ቈላ፣ ዓረባን እንዲሁም የእስራኤልን አገር ደጋውንና ቈላውን ጠቅልሎ ያዘ፤ 17እንዲሁም እስከ ሴይር በሚደርሰው ከሐላቅ ተራራ አንሥቶ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስ ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በኣልጋድ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ያዘ፤ ነገሥታታቸውንም ሁሉ ያዘ፤ መትቶም ገደላቸው። 18ኢያሱ ከእነዚህ ነገሥታት ጋር ብዙ ዘመን የፈጀ ጦርነት አደረገ። 19በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዊያውያን በስተቀር፣ ከእስራኤላውያን ጋር የሰላም ውል ያደረገ አንድም ከተማ አልነበረም፤ ሁሉንም የያዙት በጦርነት ነው። 20እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፣ ያለ አንዳች ርኅራኄ ፈጽሞ ይደመስሳቸው ዘንድ እስራኤልን እንዲወጉ ልባቸውን ያደነደነው ራሱ እግዚአብሔር ነውና።
21በዚያን ጊዜ ኢያሱ ሄዶ በተራራማው አገር፣ ማለት በኬብሮን፣ በዳቤርና በአናብ እንዲሁም በመላው የይሁዳና የእስራኤል ተራራማ አገሮች ያሉትን የዔናቅን ዘሮች ከነከተሞቻቸው በሙሉ ደመሰሳቸው። 22ከእነዚህም ጥቂቶቹ ብቻ በጋዛ፣ በጌትና በአሽዶድ ሲቀሩ፣ በእስራኤል የቀሩ የዔናቅ ዘሮች ግን አልነበሩም። 23ስለዚህ ኢያሱ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ምድሪቱን በሙሉ ያዘ፤ እንደ ነገዳቸው አከፋፈል በመመደብም ርስት አድርጎ ለእስራኤላውያን ሰጣቸው።
ከዚያም ምድርቱ ከጦርነት ዐረፈች።

Currently Selected:

ኢያሱ 11: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ