የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢዮብ 39

39
1“የበረሓ ፍየል የምትወልድበትን ጊዜ ታውቃለህን?
ዋሊያ ስታምጥስ ተከታትለህ አይተሃል?
2የእርግዝናቸው ወራት ምን ያህል እንደ ሆነ ትቈጥራለህን?
የሚወልዱበትንስ ጊዜ ታውቃለህን?
3ተንበርክከው ይወልዳሉ፤
ከምጣቸውም ጣር ይገላገላሉ።
4ግልገሎቻቸውም ይጠነክራሉ፤ በሜዳም ያድጋሉ፤
ተለይተው ይሄዳሉ፤ ወደ እነርሱም አይመለሱም።
5“ለሜዳ አህያ ነጻነት የሰጠው ማን ነው?
እስራቱንስ ማን ፈታለት?
6ምድረ በዳውን መኖሪያው፣
የጨውንም ምድር ማደሪያው አድርጌ ሰጠሁት።
7በከተማ ውካታ ይሥቃል፤
የነጂውንም ጩኸት አይሰማም።
8በየተራራው ይሰማራል፤
ሐመልማሉንም ሁሉ ለማግኘት ይወጣል።
9“ጐሽ ያገለግልህ ዘንድ ይታዘዛልን?
በበረትህስ አጠገብ ያድራልን?
10እንዲያርስልህ ልትጠምደው ትችላለህ?
ወይስ እየተከተለህ ዕርሻህን ይጐለጕልልሃልን?
11ጕልበቱ ብርቱ ስለሆነ ትተማመንበታለህ?
ከባዱን ሥራህንስ ለእርሱ ትተዋለህ?
12እህልህን እንዲሰበስብልህ፣
በዐውድማህም ላይ እንዲያከማችልህ ታምነዋለህን?
13“ሰጎን ክንፎቿን በደስታ ታራግባለች፤
ነገር ግን እንደ ሽመላ ላባዎች ሊሆኑ አይችሉም።
14ዕንቍላሏን መሬት ላይ ትጥላለች፤
እንዲሞቅም በአሸዋ ውስጥ ትተወዋለች።
15እግር እንደሚሰብረው፤
የዱር አውሬም እንደሚረግጠው አታስብም።
16የእርሷ እንዳልሆኑ ሁሉ በልጆቿ ትጨክናለች፤
ድካሟም በከንቱ ቢቀር ደንታ የላትም፤
17እግዚአብሔር ጥበብ ነሥቷታልና፤
ማስተዋልንም አልሰጣትም።
18ለመሸምጠጥም ክንፎቿን ስትዘረጋ፣
በፈረስና በጋላቢው ትሥቃለች።
19“ለፈረስ ጕልበትን ትሰጠዋለህን?
ዐንገቱንስ ጋማ ታለብሰዋለህን?
20እንደ አንበጣ የምታስዘልለው አንተ ነህን?
የማንኰራፋቱም ገናናነት አስፈሪ ነው።
21በጕልበቱ እየተመካ በብርቱ ይጐደፍራል፤
ጦርነት ሊገጥም ይወጣል።
22ያለ አንዳች ሥጋት፣ በፍርሀት ላይ ይሥቃል፤
ሰይፍ ቢመዘዝበትም ወደ ኋላ አይልም።
23ከሚብረቀረቀው ጦርና ዐንካሴ ጋር፣
የፍላጻው ኰረጆ ጐኑ ላይ ይንኳኳል።
24በወኔ መሬቱን እየጐደፈረ ወደ ፊት ይሸመጥጣል፤
የመለከት ድምፅ ሲሰማ ያቅበጠብጠዋል።
25መለከቱ ሲያንባርቅ፣ ‘ዕሠይ’ ይላል፤
የአዛዦችን ጩኸትና የሰራዊቱን ውካታ፣
ጦርነትንም ከሩቅ ያሸትታል።
26“ጭልፊት የሚበርረው፣
ክንፎቹንም ወደ ደቡብ የሚዘረጋው፣ በአንተ ጥበብ ነውን?
27ንስር ወደ ላይ የሚመጥቀው፣
ጎጆውንም በከፍታ ላይ የሚሠራው፣
በአንተ ትእዛዝ ነውን?
28በገደል ላይ ይኖራል፤ በዚያም ያድራል፤
ምሽጉም የቋጥኝ ጫፍ ነው።
29እዚያ ሆኖ የሚነጥቀውን ይቃኛል፤
ዐይኑም ከሩቅ አጥርቶ ያያል።
30ጫጩቶቹ ደም ይጠጣሉ፤
እርሱም በድን ካለበት አይታጣም።”

Currently Selected:

ኢዮብ 39: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ