ኢዮብ 32
32
ኤሊሁ
1ኢዮብ በበኩሉ ራሱን እንደ ጻድቅ ቈጥሮ ስለ ነበር፣ እነዚህ ሦስት ሰዎች ለእርሱ መልስ መስጠታቸውን ተዉ። 2ከራም ወገን የሆነው፣ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ ግን ኢዮብ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ ስላደረገ እጅግ ተቈጣው። 3ሦስቱ የኢዮብ ጓደኞች በኢዮብ ላይ መፍረድ#32፥3 የማሶሬቱ ቅጅ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ጥንታዊው የዕብራውያን ጸሐፍት ትውፊት ግን ኢዮብንም ሆነ እግዚአብሔርን ኰነኑ ይላል። እንጂ፣ ነገሩን ሊያሳምኑት ስላልቻሉ፣ በእነርሱም ላይ ተቈጣ። 4ኤሊሁ፣ ሌሎቹ በዕድሜ ይበልጡት ስለ ነበር ከእነርሱ ቀድሞ ለኢዮብ ሳይናገር ቈየ። 5ነገር ግን እነዚህ ሦስቱ የሚሉትን ባጡ ጊዜ ቍጣው ነደደ።
6ስለዚህ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ እንዲህ አለ፤
“እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፤
እናንተ ግን አዛውንቶች ናችሁ፤
ከዚህም የተነሣ የማውቀውን ለመናገር አልደፈርሁም፤
ፈርቼ ዝም አልሁ።
7‘ዕድሜ ይናገራል፤
ረዥም ዘመን ጥበብን ያስተምራል’ ብዬ ነበር።
8ነገር ግን በሰው ያለው መንፈስ፣
ሁሉን የሚችል አምላክ እስትንፋስ፣
ማስተዋልን ይሰጣል።
9ጠቢባን የሚሆኑት በዕድሜ የገፉ#32፥9 ወይም፣ ብዙ ወይም፣ ታላቅ ብቻ አይደሉም፤
የሚያስተውሉም ሽማግሌዎች ብቻ አይደሉም።
10“ስለዚህ፣ ‘ስሙኝ፣
እኔም የማውቀውን ልንገራችሁ’ እላለሁ።
11እናንተ በምትነጋገሩበት ጊዜ ታገሥሁ፤
ቃላት እየመረጣችሁ ስትናገሩ፣
በጥሞና ሰማኋችሁ፤
12በሙሉ ልብ አደመጥኋችሁ፤
ነገር ግን ከእናንተ የኢዮብን ቃል ያስተባበለ ማንም የለም፤
ለንግግሩም አጸፋ የመለሰ አልተገኘም።
13‘እኛ ጥበብ አግኝተናል፤
ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ይርታው’ አትበሉ።
14ኢዮብ ግን ቃሉን በእኔ ላይ አልሰነዘረም፤
እኔም እንደ እናንተ አነጋገር መልስ አልሰጠውም።
15“እነርሱ ተስፋ ቈርጠው የሚሉት የላቸውም፤
የሚናገሩትም ጠፍቷቸዋል።
16እንግዲህ እነርሱ መልስ ስላጡ፣
ጸጥ ብለውም ስለ ቆሙ፣ በትዕግሥት ልጠብቅን?
17እኔም የምለው ይኖረኛል፤
የማውቀውንም እገልጣለሁ።
18የምናገረው ሞልቶኛልና፤
በውስጤ ያለውም መንፈስ ገፋፍቶኛል።
19ውስጤ እንደ ተከደነና መተንፈሻ እንዳጣ የወይን ጠጅ፣
ሊፈነዳ እንደ ተቃረበም አዲስ የወይን ጠጅ አቁማዳ ሆኗል።
20ተናግሬ መተንፈስ አለብኝ፤
አፌንም ከፍቼ መልስ መስጠት ይገባኛል።
21ለማንም አላደላም፤
ሰውንም አላቈላምጥም።
22ማቈላመጥን ባውቅበትማ ኖሮ፣
ፈጣሪዬ ፈጥኖ ባጠፋኝ ነበር።
Currently Selected:
ኢዮብ 32: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.