ኢዮብ 27
27
1ኢዮብም እንዲህ ሲል ንግግሩን ቀጠለ፤
2“ፍትሕ የነሣኝ ሕያው እግዚአብሔርን!
ነፍሴንም መራራ ያደረጋት፣ ሁሉን ቻይ አምላክን!
3በውስጤ የሕይወት እስትንፋስ፣
በአፍንጫዬም ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ እስካለ ድረስ፣
4ከንፈሬ ኀጢአትን አትናገርም፤
አንደበቴም ሽንገላ አይወጣውም።
5እናንተን እንደ ቅኖች መቍጠር፣
የማላደርገው ነገር ነው፤ ጨዋነቴንም እስክሞት ድረስ አልጥልም።
6ጽድቄን አጥብቄ እይዛለሁ፤ አልለቀውምም፤
በዘመኔም ሁሉ ኅሊናዬ አይወቅሠኝም።
7“ጠላቴ እንደ በደለኛ፣
ባላንጣዬም እንደ ክፉ ይሁን።
8እግዚአብሔር ሲያስወግደው፣
ነፍሱንም ሲወስድበት ዐመፀኛ ምን ተስፋ አለው?
9በውኑ መከራ በገጠመው ጊዜ፣
እግዚአብሔር ጩኸቱን ይሰማልን?
10ሁሉን ቻይ አምላክ ደስ ይለዋልን?
ዘወትርስ እግዚአብሔርን ይጠራልን?
11“ስለ እግዚአብሔር ክንድ አስተምራችኋለሁ፤
የሁሉን ቻዩንም አምላክ ዕቅድ አልሸሽግም።
12ሁላችሁ ይህን አይታችኋል፤
ታዲያ፣ ይህ ከንቱ ንግግር ምንድን ነው?
13“እግዚአብሔር ለክፉው ሰው የመደበው ዕድል ፈንታ፣
ግፈኛም ሁሉን ቻይ አምላክ የሚቀበለው ቅርስ ይህ ነው፦
14ልጆቹ የቱንም ያህል ቢበዙም ለሰይፍ ይዳረጋሉ፤
ዘሩም ጠግቦ አያድርም።
15የተረፉለትም በመቅሠፍት ዐልቀው ይቀበራሉ፤
መበለቶቻቸውም አያለቅሱላቸውም።
16ብርን እንደ ዐፈር ቢከምር፣
ልብስንም እንደ ሸክላ ጭቃ ቢያከማች፣
17እርሱ ያከማቸውን ጻድቃን ይለብሱታል፤
ብሩንም ንጹሓን ይከፋፈሉታል።
18የሚሠራው ቤት እንደ ሸረሪት ድር፣
እህል ጠባቂም እንደ ቀለሰው መጠለያ ነው።
19ሀብታም ሆኖ ይተኛል፤ ዘለቄታ ግን የለውም፤
ዐይኑን በገለጠ ጊዜ ሀብቱ ሁሉ በቦታው የለም።
20ድንጋጤ እንደ ጐርፍ ድንገት ያጥለቀልቀዋል፤
ዐውሎ ነፋስም በሌሊት ይዞት ይሄዳል።
21የምሥራቅ ነፋስ ይወስደዋል፤ እርሱም አይገኝም፤
ከስፍራውም ይጠርገዋል።
22ከነፋሱ ብርታት ለማምለጥ ይሮጣል፤
ነገር ግን እየተወረወረ ያለ ርኅራኄ ይደርስበታል፤
23እጁንም እያጨበጨበ ያሾፍበታል፤
በፉጨትም ከስፍራው ያሽቀነጥረዋል።”
Currently Selected:
ኢዮብ 27: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.