የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢዮብ 10

10
1“ሕይወቴን እጅግ ጠላሁ፤
ስለዚህም ማጕረምረሜን ያለ ገደብ እለቅቃለሁ፤
በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ።
2እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ፤
በምን ላይ እንዳልተስማማን ንገረኝ እንጂ አትፍረድብኝ።
3የክፉዎችን ዕቅድ በደስታ እየተቀበልህ፣
እኔን ግን ስታስጨንቀኝ፣
የእጅህንም ሥራ ስታዋርድ ደስ ይልሃልን?
4አንተ ዐይንህ የሥጋ ለባሽ ዐይን ነውን?
ሟች የሆነ የሰው ልጅ እንደሚያይ ታያለህን?
5ዘመንህ እንደ ሟች ሰው ዘመን ነውን?
ወይስ ዓመታትህ እንደ ሰው ዓመታት ናቸውን?
6ታዲያ፣ በደልን የምትፈላልግብኝ፣
ኀጢአቴንም የምትከታተለው ለምንድን ነው?
7እኔ በደለኛ እንዳልሆንሁ፣
ከእጅህም ሊያስጥለኝ ማንም እንደማይችል አንተ ታውቃለህ።
8“እጅህ አበጀችኝ፤ ሠራችኝም፤
መልሰህ ደግሞ ታጠፋኛለህን?
9እንደ ሸክላ እንዳበጀኸኝ ዐስብ፤
አሁን ደግሞ ወደ ትቢያ ትመልሰኛለህን?
10እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን?
እንደ እርጎስ አላረጋኸኝምን?
11ቈዳና ሥጋ አለበስኸኝ፤
በዐጥንትና በጅማትም አገጣጥመህ ሠራኸኝ።
12ሕይወትን ሰጠኸኝ፤ በጎነትንም አሳየኸኝ፤
እንክብካቤህም መንፈሴን ጠበቀ።
13“ይህን ሁሉ ግን በልብህ ሸሸግህ፤
ነገሩ በዐሳብህ እንደ ነበር ዐውቃለሁ፤
14ኀጢአትን ብሠራ ትመለከተኛለህ፤
መተላለፌንም ሳትቀጣ አታልፍም።
15በደለኛ ብሆን ወዮልኝ፤
ንጹሕ ብሆንም፣ ራሴን ቀና አላደርግም፤
ውርደትን ተከናንቤአለሁና፤
በመከራም ተዘፍቄአለሁ።#10፥15 ወይም መከራዬን ዐውቄአለሁ
16ራሴን ከፍ ከፍ ባደርግ፣ እንደ አንበሳ ታደባብኛለህ፤
አስፈሪ ኀይልህን ደጋግመህ ታሳየኛለህ፤
17አዳዲስ ምስክሮችን ታመጣብኛለህ፤
ቍጣህንም በላዬ ትጨምራለህ፤
ሰራዊትህም ተከታትሎ ይመጣብኛል።
18“ታዲያ ለምን ከማሕፀን አወጣኸኝ?
ምነው ዐይን ሳያየኝ በሞትሁ ኖሮ!
19ምነው ባልተፈጠርሁ!
ወይም ከማሕፀን ቀጥታ ወደ መቃብር በወረድሁ!
20ጥቂት የሆነው ዘመኔ እያለቀ አይደለምን?
ከሥቃዬ ፋታ እንዳገኝ ተወት አድርገኝ፤
21ወደማልመለስበት ስፍራ፣
ወደ ጨለማና ወደ ሞት ጥላ#10፥21 ወይም ከባድ ጥላ እንዲሁም 22 አገር ከመሄዴ በፊት፣
22ብርሃኑ እንደ ጨለማ ወደ ሆነበት፣
የሞት ጥላ ወዳረበበበት፣ ሥርዐት የለሽ ወደ ሆነ ምድር፣
ድቅድቅ ጨለማ ወደ ሰፈነበት አገር ሳልሄድ ተወኝ።”

Currently Selected:

ኢዮብ 10: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ