ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር እንደ ገና ለደቀ መዛሙርቱ ታየ፤ በዚህም ሁኔታ ተገለጠ፤ ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፣ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱ ሌሎች ሁለት አንድ ላይ ነበሩ፤ ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው፤ እነርሱም፣ “እኛም ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ጀልባዋ ገቡ፤ በዚያ ሌሊት ግን ምንም አላጠመዱም። ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር። እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የለንም” አሉት። እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተ ቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወድደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ጌታ እኮ ነው!” የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘልሎ ወደ ባሕሩ ገባ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ። ወደ ምድርም በደረሱ ጊዜ፣ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም፣ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ እስቲ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ አምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደ ሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም። ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤ እንዲሁም ዓሣውን። እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
ዮሐንስ 21 ያንብቡ
ያዳምጡ ዮሐንስ 21
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዮሐንስ 21:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos