ኤርምያስ 52
52
የኤርምያስ ቃል እዚህ ላይ ይፈጸማል።
የኢየሩሳሌም መውደቅ
52፥1-3 ተጓ ምብ – 2ነገ 24፥18-20፤ 2ዜና 36፥11-16
52፥4-16 ተጓ ምብ – ኤር 39፥1-10
52፥4-21 ተጓ ምብ – 2ነገ 25፥1-21፤ 2ዜና 36፥17-20
1ሴዴቅያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ የእናቱም ስም አሚጣል ነበረ፣ እርሷም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 2ሴዴቅያስም ኢዮአቄም እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ። 3እንግዲህ ይህ ሁሉ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሊደርስ የቻለው ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ነበር፤ በመጨረሻም ከፊቱ አስወገዳቸው።
በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።
4ስለዚህ ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሰራዊቱን ሁሉ አስከትቶ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ ከተማዪቱንም ከበቧት፤ በዙሪያውም የዐፈር ድልድል ሠሩ። 5ከተማዪቱም እስከ ንጉሥ ሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት ዐሥራ አንደኛ ዓመት ድረስ እንዲሁ እንደ ተከበበች ቈየች።
6በአራተኛው ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማዪቱ ራብ ጸንቶ ስለ ነበር ሕዝቡ የሚበላውን ዐጣ፤ 7የከተማዪቱም ቅጥር ተነደለ፤ ሰራዊቱም ሁሉ ኰብልሎ ሄደ። ባቢሎናውያን#52፥7 ወይም ከለዳውያን፤ 17 ይመ። በከተማዪቱ ዙሪያ ቢኖሩም፣ በንጉሡ የአትክልት ስፍራ አጠገብ በሁለት ቅጥሮች መካከል ባለው በር በሌሊት ከተማዪቱን ጥለው ሸሹ፤ ወደ ዓረባም#52፥7 ወይም ዮርዳኖስ ሸለቆ አመሩ። 8የባቢሎናውያንም#52፥8 ወይም ከለዳውያን፤ 14 ይመ። ሰራዊት ንጉሥ ሴዴቅያስን ተከታትሎ በማሳደድ በኢያሪኮ ሜዳ ደረሱበት፤ ወታደሮቹም ሁሉ ከርሱ ተለይተው ተበታትነው ሳለ፣ ንጉሡን ያዙት።
9በዚያ ጊዜ በሐማት ምድር በሪብላ ወደ ነበረው ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ በዚያም የባቢሎን ንጉሥ ፈረደበት። 10በሪብላም የባቢሎን ንጉሥ፣ የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች በአባታቸው ፊት ገደላቸው፤ የይሁዳንም ባለሥልጣኖች ሁሉ ገደላቸው፤ 11የሴዴቅያስንም ዐይኖች አወጣ፤ በናስ ሰንሰለትም አሰረው። የባቢሎንም ንጉሥ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ በዚያም እስከ ዕለተ ሞቱ በእስር ቤት አቈየው።
12የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት በዐምስተኛው ወር፤ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፣ የባቢሎን ንጉሥ ባለሟል የክብር ዘበኞች አዛዥ የነበረው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 13የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ፣ ቤተ መንግሥቱን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የሚገኙትን ቤቶች ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ እያንዳንዱንም ትልልቅ ሕንጻዎችንም በእሳት አወደመ። 14በክብር ዘበኞቹ አዛዥ ሥር የነበሩት የባቢሎናውያን ሰራዊት ሁሉ በኢየሩሳሌም ዙሪያ ያለውን ቅጥር በሙሉ አፈረሱ። 15የክብር ዘቡ አዛዥ ናቡዘረዳን አንዳንድ የድኻ ድኾችንና በከተማዪቱ የቀረውን ሕዝብና ሸሽተው ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን ሰዎች#52፥15 ወይም ተራው ሕዝብ ከእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ጋራ አፈለሳቸው። 16ሆኖም የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን ሌሎች የምድሪቱን ድኾች፣ ወይን ተካዮችና ዐራሾች እንዲሆኑ አስቀራቸው።
17ባቢሎናውያን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበሩትን የናስ ዐምዶች፣ ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎችንና ከናስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ ሰባበሩ፤ ናሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱ። 18ከእነዚህም ሌላ ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መኰስተሪያዎቹን፣ ወጭቶቹን፣ ጭልፋዎቹንና ለቤተ መቅደስ አገልግሎት የሚውሉትን የናስ ዕቃዎች በሙሉ ወሰዱ። 19የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ጐድጓዳ ሳሕኖችን ጥናዎችን፣ ወጭቶችን፣ ምንቸቶችን፣ መቅረዞችን፣ ጭልፋዎችንና ለመጠጥ ቍርባን ማቅረቢያ የሚሆኑ ወጭቶችን ይዞ ሄደ።
20ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከናስ ያሠራቸው፦ ሁለቱ ዐምዶች፣ ትልቁ የውሃ ገንዳ፣ ከሥሩ ያሉት ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችና ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎች ክብደታቸው ከሚዛን በላይ ነበር። 21እያንዳንዱም ዐምድ ከፍታው ዐሥራ ስምንት ክንድ ዙሪያ ክቡም#52፥21 ከፍታው 27 ጫማ (8.1 ሜትር) እና ዙሪያ ክቡ 18 ጫማ (5.4 ሜትር) ገደማ ነው። ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ ውስጡ ክፍት ስለ ሆነ የእያንዳንዱ ከንፈር ውፍረት አራት ጣት ነበረ። 22በአንዱ ዐምድ ዐናት ላይ ያለው የናስ ጕልላት ቁመት ዐምስት ክንድ#52፥22 7½ ጫማ (2.3 ሜትር) ገደማ ነው። ሲሆን፣ ዙሪያውንም ሁሉ የሮማን ቅርጽ ባላቸው የናስ ጌጣጌጦች የተዋበ ነበር፤ ሌላውም ዐምድ የሮማኑን ጌጣጌጥ ጨምሮ ከዚሁ ጋራ ተመሳሳይ ነበር። 23ዘጠና ስድስቱ ሮማኖች ከጐን በቀላሉ የሚታዩ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ በዙሪያው ካለው ጌጥ በላይ ያለው የሮማኖች ቍጥር አንድ መቶ ነበር።
24የክብር ዘበኞቹ አዛዥም ሊቀ ካህኑን ሠራያን፣ በማዕርግ ከርሱ ቀጥሎ ያለውን ካህኑን ሶፎንያስንና ሦስቱን የበር ጠባቂዎች አስሮ ወሰዳቸው፤ 25በከተማው ውስጥ ከቀሩትም ሕዝብ፣ የተዋጊዎቹ ኀላፊ የነበረውን መኰንን፣ ሰባቱን የንጉሡን አማካሪዎች ከአገሬው ሕዝብ ወታደር የሚመለምለውን መኰንን ጸሓፊና በከተማው ውስጥ የተገኙትን ሌሎች ስድሳ ሰዎች ወሰደ። 26የክብር ዘበኞቹ አዛዥ ናቡዘረዳን እነዚህን ሁሉ ይዞ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ነበረበት ወደ ሪብላ አመጣቸው። 27ንጉሡም ሰዎቹን በሐማት ምድር በነበረችው በሪብላ ውስጥ አስገደላቸው።
ይሁዳም ከምድሩ በዚህ ሁኔታ ተማርኮ ሄደ።
28ናቡከደነፆር ማርኮ የወሰደው ሕዝብ ቍጥር እንደሚከተለው ነው፦
በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣
ሦስት ሺሕ ሃያ ሦስት አይሁድ፤
29ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣
ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ሰዎች ከኢየሩሳሌም፤
30ናቡከደነፆር በነገሠ በሃያ ሦስተኛው ዓመት፣
የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን፣ ሰባት መቶ አርባ ዐምስት አይሁድ ማርኮ ወስዷል።
በአጠቃላይ አራት ሺሕ ስድስት መቶ ሰዎች ነበሩ።
የዮአኪን መፈታት
31የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት፣ ዮርማሮዴክ#52፥31 እንዲሁም አሜልማርዱክ ተብሎ ይጠራል። በባቢሎን ነገሠ፤ በዚሁ ዓመት፣ በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ ዐምስተኛው ቀን የይሁዳን ንጉሥ ዮአኪንን ዐሰበው፤ ከእስር ቤትም አወጣው፤ 32በመልካምም ቃል አናገረው፤ ከርሱም ጋራ በባቢሎን በምርኮ ከነበሩት ነገሥታት ይልቅ ከፍ ባለ የክብር ቦታ አስቀመጠው። 33ዮአኪንም የእስር ቤት ልብሱን ጣለ፤ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ከንጉሡ ማእድ ዘወትር ይመገብ ነበር። 34የባቢሎንም ንጉሥ፣ ዮአኪን እስኪሞት ድረስ፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሳያቋርጥ በየዕለቱ ቀለቡን ይሰጠው ነበር።
Currently Selected:
ኤርምያስ 52: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.