ኤርምያስ 29
29
በምርኮ ላሉት የተላከ ደብዳቤ
1ነቢዩ ኤርምያስ በምርኮ ተወስደው በሕይወት ለቀሩት ሽማግሌዎች፣ ለካህናቱ፣ ለነቢያቱና ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ለወሰዳቸው ሕዝብ ሁሉ የላከው የደብዳቤ ቃል ይህ ነው፤ 2ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያን#29፥2 ኢኮንያን የኢዮአኪን ሌላው አቻ ስም ነው እቴጌዪቱ እናቱ፣ የቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም መሪዎች፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ብረት ቀጥቃጮች ተማርከው ከኢየሩሳሌም ከተወሰዱ በኋላ ነበር። 3ደብዳቤውንም ከይሁዳ ንጉሥ ከሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር በተላኩት መልእክተኞች በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ላከው፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፤
4የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረካቸው ሁሉ እንዲህ ይላል፤ 5“ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልት ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ፤ 6አግብታችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ውለዱ፤ ወንዶች ልጆቻችሁንና ሴቶች ልጆቻችሁን አጋቡ፤ እነርሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ይውለዱ፤ ቍጥራችሁም በዚያ ምድር ይብዛ እንጂ አይነስ። 7ተማርካችሁ ለሄዳችሁባት ከተማ ሰላምና ብልጽግናን እሹ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልዩላት፤ ምክንያቱም እርሷ ብትበለጽግ እናንተም ትበለጽጋላችሁ።” 8የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በርግጥ እንዲህ ይላልና፤ “በመካከላችሁ ያሉት ነቢያትና ጠንቋዮች አያታልሏችሁ፤ የሚያልሙላችሁንም ሕልም አትስሙ፤ 9በስሜ ሐሰተኛ ትንቢት ይነግሯችኋል እንጂ እኔ አልላክኋቸውም” ይላል እግዚአብሔር።
10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። 11ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም። 12እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ቀርባችሁ ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ። 13እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ፤ 14እኔም እገኝላችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከምርኮም#29፥14 ወይም ዕድል ፈንታችሁን እመልስላችኋለሁ እመልሳችኋለሁ፤ እናንተንም ከበተንሁበት አገርና ስፍራ ሁሉ እመልሳችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በምርኮ ምክንያት ወዳስለቀቅኋችሁም ምድር እመልሳችኋለሁ።”
15እናንተም፣ “እግዚአብሔር በባቢሎን ነቢያት አስነሥቶልናል” ትላላችሁ፤ 16እግዚአብሔር ግን በዳዊት ዙፋን ላይ ስለሚቀመጠው ንጉሥና ከእናንተ ጋራ ተማርኮ ስላልሄደው ወገንህ በዚህ ከተማ ስለ ቀረው ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ይላል፤ 17የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በርግጥ እንዲህ ይላል፤ “ሰይፍን፣ ራብንና መቅሠፍትን እሰድድባቸዋለሁ፤ ከመበላሸቱ የተነሣም ሊበላ እንደማይቻል እንደ መጥፎ የበለስ ፍሬ አደርጋቸዋለሁ። 18በሰይፍ፣ በራብና በመቅሠፍት አሳድዳቸዋለሁ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ፊት የሚያስጸይፉ አደርጋቸዋለሁ፤ በማሳድድባቸውም ሕዝቦች ዘንድ የርግማንና#29፥18 ይህ ማለት ስማቸው ለመርገም የሚውል ይሆናል (29፥22 ይመልከቱ)፤ ወይም ሌሎች የተረገሙ መሆናቸውን ይመለከታሉ። የድንጋጤ፣ የመሣቂያና የመዘባበቻ ምልክት ይሆናሉ፤ 19በአገልጋዮቼ በነቢያት በኩል ደጋግሜ የላክሁላቸውን ቃሌን አልሰሙምና” ይላል እግዚአብሔር፤ “እናንተ ምርኮኞችም አልሰማችሁም” ይላል እግዚአብሔር።
20ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን የሰደድኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 21የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚነግሯችሁ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ እንዲህ ይላል፤ “እነዚህን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም ዐይናችሁ እያየ ይገድላቸዋል። 22በእነርሱ ላይ ከደረሰው የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ፣ ‘እግዚአብሔር፣ የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ ያድርግብህ’ ብለው ይራገማሉ፤ 23ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ጋራ በማመንዘርና ያልነገርኋቸውን ቃል በስሜ በሐሰት በመናገር በእስራኤል ዘንድ በደል ፈጽመዋልና። ይህንም እኔ ዐውቃለሁ፤ ምስክር ነኝ” ይላል እግዚአብሔር።
ለሸማያ የተላከ መልእክት
24ለኔሔላማዊው ለሸማያ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ 25“የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በኢየሩሳሌም ላለው ሕዝብ ሁሉ፣ ለካህኑ ለመዕሤያ ልጅ ለሶፎንያስና ለሌሎችም ካህናት ሁሉ በገዛ ስምህ ደብዳቤዎችን ልከሃል፤ ለሶፎንያስም እንዲህ ብለሃል፤ 26‘በእግዚአብሔር ቤት ኀላፊ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር በካህኑ በዮዳሄ ምትክ ካህን አድርጎ ሾሞሃል፤ ነቢይ ነኝ እያለ ትንቢት የሚናገር ማንኛውም ያበደ ሰው እግሩን በግንድ፣ ዐንገቱን በሰንሰለት መቀፍደድ ይገባሃል። 27ታዲያ፣ ነቢይ ነኝ ባዩን የዓናቶቱን ኤርምያስን ለምን አልገሠጽኸውም? 28ይህ ሰው፣ “የምርኮው ጊዜ ረዥም ስለ ሆነ፣ ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልትም ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ” በማለት ወደ ባቢሎን መልእክት ልኮብናል።’ ”
29ካህኑ ሶፎንያስም ደብዳቤውን ለነቢዩ ኤርምያስ አነበበለት። 30የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 31“ይህን መልእክት በምርኮ ላሉት ሁሉ እንዲህ ብለህ ላክ፤ ‘ስለ ኔሔላማዊው ስለ ሸማያ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ ሳልልከው ሸማያ ትንቢት ተናግሮላችሁ፣ በሐሰት እንድትታመኑ አድርጓችኋልና፣ 32እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ኔሔላማዊውን ሸማያንና ዘሩን እቀጣለሁ፤ በእኔ ላይ ዐመፅን ተናግሯልና፣ በዚህ ሕዝብ መካከል የሚተርፍ ዘር አይኖረውም” ይላል እግዚአብሔር፤ ለሕዝቤ የማደርገውንም መልካም ነገር አያይም።’ ”
Currently Selected:
ኤርምያስ 29: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.