ኤርምያስ 21
21
ለንጉሥ ሴዴቅያስ የተሰጠ ምላሽ
1የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ፣ የመልክያን ልጅ ፋስኮርን እንዲሁም የመዕሤያን ልጅ ካህኑን ሶፎንያስን ወደ እርሱ በላከ ጊዜ፣ ቃል ከእግዚአብሔር ወደ ኤርምያስ መጣ፤ የተላኩትም እንዲህ ብለውት ነበር፤ 2“የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር#21፥2 ናቡከደነፆር አቻ የሆነው የዕብራይስጡ ናቡከደነፆር በዚህ ክፍልና ብዙ ጊዜ በኤርምያስና ሕዝቅኤል መጽሐፍ ይገኛል። ሊወጋን ስለ ሆነ፣ እባክህን ፈጥነህ፣ እግዚአብሔርን ጠይቅልን፤ ምናልባት ንጉሡ ከእኛ ይመለስ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ቀድሞው ታምራት ያደርግልን ይሆናል” ብለው ነበር።
3ኤርምያስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ለሴዴቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤ 4‘የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከቅጥሩ ውጭ የከበቧችሁን የባቢሎንን ንጉሥና ባቢሎናውያንን#21፥4 ወይም ከለዳውያን፤ 9 ላይ ይመ። ለመውጋት በእጃችሁ የያዛችሁትን የጦር መሣሪያ በእናንተው ላይ አዞራለሁ፤ ወደዚህችም ከተማ ሰብስቤ አስገባቸዋለሁ። 5እኔ ራሴ ለቅጣት በተዘረጋ እጅና በብርቱ ክንድ፣ በቍጣና በመዓት፣ በታላቅም መቅሠፍት እወጋችኋለሁ። 6በዚህች ከተማ የሚኖሩትን፣ ሰዎችንም ሆኑ እንስሳትን እመታለሁ፤ እነርሱም በታላቅ መቅሠፍት ይሞታሉ። 7ከዚያ በኋላ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና መኳንንቱን፣ ከመቅሠፍት፣ በከተማው ከሰይፍና ከራብ የተረፈውንም ሕዝብ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆርና ሕይወታቸውን ለማጥፋት ለሚሹ ጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፤ አይራራላቸውም፤ አይምራቸውምም።’
8“በተጨማሪም ለዚህ ሕዝብ እንዲህ በል፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ በፊታችሁ አድርጌአለሁ፤ 9በዚህች ከተማ የሚቈይ ሁሉ በሰይፍ፣ በራብና በመቅሠፍት ይሞታል፤ ወጥቶ ለከበቧችሁ ባቢሎናውያን እጁን የሚሰጥ ግን ነፍሱን ያተርፋል፤ በሕይወትም ይኖራል። 10በዚህች ከተማ ላይ በጎ ሳይሆን ክፉ ለማድረግ ወስኛለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር፤ ለባቢሎን ንጉሥ ትሰጣለች፤ እርሱም በእሳት ያጠፋታል።’
11“ለይሁዳ ንጉሥ ቤትም እንዲህ በል፤ ‘የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ 12የዳዊት ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ ‘ካደረጋችሁት ክፋት የተነሣ፣
ቍጣዬ እንዳይቀጣጠል፣
ማንም ሊያጠፋው እስከማይችል እንዳይነድድ፣
በየማለዳው ፍትሕን አድርጉ፤
የተበዘበዘውን ሰው፣
ከጨቋኙ እጅ አድኑት።
13ከሸለቆው በላይ፣
በድንጋያማው ዐምባ ላይ የምትኖሪ ሆይ፤
እኔ በአንቺ ላይ ወጥቻለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።
“ማን በእኛ ላይ ይወጣል?
ማንስ ወደ መኖሪያችን ደፍሮ ይገባል?” የምትሉ ሆይ፤
14እንደ ሥራችሁ መጠን እቀጣችኋለሁ፤
ይላል እግዚአብሔር፤
በዱሯም እሳት እለኵሳለሁ፤
በዙሪያዋ ያለውንም ሁሉ ይበላል።’ ”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.